ፊልም ለመቅረጽ ሲል የጎዳና ተዳዳሪዎችን መርዝ ያበላው ሰው በቁጥጥር ሥር ዋለ

አሜሪካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ ካሊፎርኒያ አንድ ግለሰብ ስምንት የጎዳና ተዳዳሪዎችን አፍዝ አድንግዝ እጽ በምግብ ለውሶ ሰጥቷቸዋል፡፡

ዊሊያም ሮበርት ኬብል የ38 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ይህን አደንዛዥ መርዝ ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ ከሰጣቸው በኋላ ሲሰቃዩ እርሱ ይቀርጻቸው ነበር ተብሏል፡፡የጎዳና ተዳዳሪዎቹ በተመገቡት የተመረዘ ምግብ የተነሳ ሆስፒታል ነው የሚገኙት፡፡

ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ 19 ዓመት ዘብጥያ ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡የኦሬንጅ ወረዳ የሕግ ጠበቃ ቶድ ስፒዘር እንደተናገሩት ተከሳሹ እነዚህን ሰዎች የመረጣቸው ድህነታቸውን ተጠቅሞ ነው፡፡

የነርሱን ስቃይ በካሜራ ቀርጾ እርሱ ለመዝናኛነት ሊያውለው ነው ያሰበው፤ ይህ ጭካኔ ነው ብለዋል ቶድ፡፡በካሊፎርኒያ የኦሬንጅ ወረዳ አቃቢ ሕግ እንዳብራራው ተከሳሹ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ያገኛቸው በሀንቲግተን የባሕር ዳርቻ ሲሆን ምግብ እንደሚፈልጉ ከጠየቃቸው በኋላ አዎ ሲሉት የተመረዘ ምግብ አቀብሏቸዋል።

አንዳንዶቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተከሳሹ የሚያቃጥል ምግብ ውድድር እያደረኩ ነው፣ ቶሎ የጨረሰ ይሸለማል በሚል አታልሎ እንደቀረጻቸው ተናግረዋል፡፡

ያቀረበላቸው የተመረዘ ምግብ በአደገኛ በርበሬና ቃሪያ የተሰነገና እጅግ የሚያቃጥል ነው ተብሏል፡፡ምግቡን ከቀመሱ በኋላ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ግማሾቹ ራሳቸውን የሳቱ ሲሆን ቀሪዎቹ ለመተንፈስ ተቸግረው ታይተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ሲያስመልሳቸው ነበር፡፡

ተከሳሹ አሁን በግማሽ ሚሊዮን ዶላር ዋስ የተለቀቀ ሲሆን ባፈለው ወር ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡አቃቢ ሕግ በሰውየው ላይ 8 ክሶችን አቅርቦበታል፡፡ ከጎዳና ተዳዳሪዎቹ አንዱ ሽማግሌ ሲሆኑ ትንንሽ ልጆችም ይገኙበታል፡፡ ይህም ክሱን ያጠናክርበታል፡፡

ባለፈው ዓመት አንድ ስፔናዊ የዩቲዩብ አሰናጅ በተመሳሳይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን አትታሎ ኦሪዮ ብስኩት እያስበላ ቀርጻ ሲያደርግ ነበር፡፡ ብስኩቱ ተለውሶ የነበረው ደግሞ በጥርስ ሳሙና ፈሳሽ ነበር፡፡ይህ ሰው 15 ወራት ተፈርዶበት ዘብጥያ ወርዷል፡፡