በኮሮና የሟች ቤተሰቦች የጣሊያኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊከሱ እየተዘጋጁ ነው

ጣሊያን

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

በኮሮና የሟች ቤተሰቦች የጣሊያኑን ጠ/ሚኒስትር ሊከሱ እየተዘጋጁ ነው።

በሰሜን ጣሊያን አቃቢ ሕግ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፔ ኮንቴን ዛሬ አርብ ለምርመራ ቀጥሯቸዋል።

ምክንያቱ ደግሞ ዘመድ ወዳጆቻቸው በኮሮና የሞቱባቸው ቤተሰቦች "መንግሥት ቶሎ እርምጃ አልወሰደም፤ ተዘናግቶ ነበር፣ ቤተሰቦቻችንን በሞት ያጣነው በመንግሥት እንዝላልነት ነው" የሚል ክስ በማቅረባቸው ነው።

አቃቢ ሕግ በዛሬው ቀጠሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በወረርሽኙ የመጀመርያ ቀናት ስለተወሰዱና መወሰድ ስለነበረባቸው እርምጃዎች በጥያቄ ያስጨንቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በሰሜን ጣሊያን አቃቢ ሕግ የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ያሰናዳ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠየቁትም ከሚላን ከተማ በቅርብ በምትገኘው በበርጋሞ ከተማ ተገኝተው ይሆናል፡፡በርጋሞ ኮሮናቫይረስ መጀመርያ የተነሳባት የሰሜን ጣሊያን ከተማ ናት።

ቫይረሱ ከበርጋሞ ተነስቶ ነው ጣሊያንንም ሆነ አውሮጳን ያዳረሰው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ ለዚህ ምርመራ ዝግጁ እንሆኑና በጭራሽ እንዳልተጨነቁበት ተናግረዋል።

"ዜጎች የማወቅ መብት አላቸው፣ መንግሥታቸውን የመጠየቅ መብት አላቸው፤ እኛም የመመለስ መብት አለን፤ ምንም አልፈራሁም" ብለዋል፡፡

የሟች ቤተሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቫይረሱ የከፋባቸውን ስፍራዎች ቀድመው መከለል ሲገባቸው ይህን አላደረጉም፤ ተዘናግተው ነበር ብለው ነው የሚከሷቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ ባለፈው ሚያዚያ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጣሊያን ለደረሰው ሞት ቶሎ እርምጃ ባለመውሰዳቸውና ነገሩን አቅልለው በማየታቸው ተጠያቂ ይሆኑ ወይ በሚል ተጠይቀው ሲመልሱ አስተባብለው ነበር፡፡

"ወረርሽኙ እንደጀመረ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥዬ ቢሆን ኖሮ ሕዝቤ እብድ አድርጎ ነበር የሚመለከተኝ" ብለው ነበር በዚያ ቃለ ምልልስ፡፡

50 የሚሆኑ ክሶች ትናንት ሐሙስ በበርጋሞ የአቃቢ ሕግ ቢሮ ፋይል ተከፍቶላቸዋል፡፡ ክሶቹን ያጠናቀረው ደግሞ ኖይ ዴኑንቼርሞ የተሰኘ የዜጎች ተቆርቋሪ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን ቤተሰቦቻቸው በኮቪድ-19 የሞቱባቸውን ቤተሰቦች የያዘ ነው፡፡

ከሳሾች እንደሚሉት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደጀመረ በሎምባርዴ አልዛኖና ኔምብሮ ከተሞች ‹‹አደገኛ አካባቢ›› በሚል ሊዘጉ ይገባ ነበር፡፡ ከሳሾቹ ያ ተደርጎ ቢሆን ዘመድ ቤተሰቦቻችን አይሞቱብንም ነበር ብለው ያምናሉ፡፡

የክስ የመጀመርያ ምዕራፍ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለጥያቄ የመጥራት ሂደት ከወረርኙ ጋር በተያያዘ በአውሮጳ መንግሥት ላይ ያነጣጠረ የመጀመርያው የክስ ፋይል ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ያም ሆኖ የሎምባርዲ ክልል የሚተዳደረው በቀኝ አክራሪዎች ነው፡፡ በእንዝላልነት ከተከሰሱም ሊጠየቁ የሚገባው ክልሉን የሚያስተዳድሩት የአክራሪ ተቃዋሚ ፓርቲ መሆን ሲገባው ለምን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳነጣጠረ ግልጽ አይደለም፡፡

በርካታ የክልሉ ነዋሪዎችም ለደረሰው ሞት ተጠያቂ አድርገው የሚያስቡት ከማእከላዊ መንግሥት ይልቅ የክልሉን አስተዳዳሪዎች ነው፡፡አቃቢ ሕግ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን ሉሲያና ላሞርጌሴን እንዲሁም የጤና ሚኒስትሩን ሮቤርቶ ስፔራንዛን ለጥያቄ ጠርቷቸዋል፡፡

ይህ አቃቢ ሕግ የጠራው የጥያቄና ምርመራ ጉዳዩን ወደተሟላ የክስ ሂደት ለመውሰድ በቂ ማስረጃዎች ካሉ ለመወሰን የሚያስችል ነው፡፡ ሎምባርዴ ክልል መጀመርያ ወረርሽኙ የተነሳበት ቦታ ሲሆን ወደ አውሮጳ የተዛመተውም ከዚሁ ተነስቶ ነው፡፡

ከጣሊያን ግማሹ የሞተው በዚሁ ክልል ነዋሪ የሆነ ነው፡፡እስከ ትናን ድረስ በጣሊያን የሟቾች ቁጥር 34ሺ 114 ነበር፡፡ ይህ አሐዝ ጣሊያንን በአውሮጳ ከዩናይትድ ኪንግደም ቀጥላ ሁለተኛ፣ በዓለም ደግሞ አራተኛ ተጎጂ አገር ያደርጋታል፡፡