በኬንያ የተቆጡ ሰልፈኞች የፖሊስ ካምፕን በእሳት አወደሙ

በኬንያ የተቆጡ ሰልፈኞች የፖሊስ ካምፕ በእሳት አያያዙ

የፎቶው ባለመብት, AFPCopyright

ከኬንያ መዲና ናይሮቢ በምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው ናይቫሻ ከተማ ፖሊስ የሚያደርሰውን ጥቃት ለመቃወም አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች የፖሊስ ካምፕ በእሳት አጋዩ።

ነዋሪዎቹ የፖሊስ ካምፑን በእሳት ካያያዙ በኋላ እሳቱ ተቀጣጥሎ ወደ ሌሎች ቤቶች ተዛምቶ ነበር።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች በቦታው ደርሰው እሳቱን የተቆጣጠሩት ሲሆን በአደጋው ዋጋው ያልታወቀ ንብረት መውደሙ ተገልጿል።

የእሳት አደጋው በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ እና ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን የናይቫሻ ፖሊስ ኮሚሽነር ማቲኦያ ምቦጎ ገልጸዋል።

ፖሊስ እስካሁን ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ያላዋለው ተጠርጣሪ የሌለ ሲሆን እሳቱን ማን እንዳስነሳው በቅርቡ እንደርስበታለን ብሏል።

በኬንያ የፖሊስን የኃይል ድርጊት የሚመረምር አንድ ገለልተኛ አካል ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት በአገሪቱ የፖሊስ ጭካኔያዊ እርምጃ እየጨመረ መጥቷል።

ይህ ገለልተኛ አካል እንዳለው ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ መንግሥት የጣለውን የሰዓት እላፊን ጨምሮ ሌሎች ገደቦችን ለማስፈጸም የተሰማራ የፖሊስ ኃይል 15 ሰዎችን ገድሏል ብሏል።

ድርጊቱን የፈጸሙት የፖሊስ አባላትም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንዲጀመርባቸው ጠይቋል።

ባሳለፍነው እሁድም ሦስት የፖሊስ አባላት የ21 ዓመቷን ተጠርጣሪ ከሞተር ሳይክል ጋር አስረው መሬት ላይ ሲጎትቱ መታየታቸው በኬንያ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። ወጣቷን ከሞተር ሳይክል ጋር አስረው መሬት ላይ የጎተቱት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

አንዱ የፖሊስ አባል ሞተር ሳይክሉን ሲያሽከረክር፣ ሌላኛው ደግሞ ወጣቷን ሲገረፍ ሦስተኛው የፖሊስ አባል ድግሞ ድርጊቱን በሞባይል ስልኩ ሲቀርጽ ነበር።

በስርቆት ወንጀል ተባባሪ ነሽ ተብላ የተጠረጠረችው ሜርሲ ቼሪኖ፤ ሦሰቱ የፖሊስ አባላት ከሚፈጽሙባት የሰቆቃ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ስትማጸን ነበር።