ቀጣዩ 8.5 በመቶ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እድገት በባለሙያዎች ዕይታ

graph

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደሚያደርገው በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ፅህፈት ቤት አዳራሽ ሐሙስ ሰኔ አራት ቀን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ 476.1 ቢሊዮን ብር ገደማ ይሆናል በተባለው በቀጣዩ የበጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቷል።

ከዚሁ ውስጥ በመንግሥት ረቂቅ በጀት መሰረት 176 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆነው ለክልሎች የሚሰጥ ሲሆን፤ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ ለመደበኛ ወጪዎቹ 133 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎቹ 160 ቢሊዮን ብር ይደርሰዋል መባሉን የአገር ውስጥ የብዙሃን መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል።

ረቂቅ በጀቱን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት የፌዴራል መንግሥቱ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ቀጣዩ የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ 8.5 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያ 9 በመቶ የምጣኔ ሃብት ዕድገትን እጠብቃለሁ ብላ ነበር።

ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት ምጣኔ ሃብት ላይ ከባድ የሚባል ጫናን እየፈጠረ ባለበትና የዚህ በሽታ ተጽዕኖ ለዓመታት ባይሆን ለቀጣይ ረዥም ወራት እንሚቀጥል እየተነገረ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዚህ መጠን ሊያድግ የሚችልበት ዕድል መኖሩ እያነጋገረ ነው።

የቀጣዩን የበጀት ዓመት የአገሪቱን በጀትና ተጠባቂ ዕድገትን በተመለከተ ቢቢሲ የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎቹን አለማየሁ ገዳን (ዶ/ር) እና አቶ ዋሲሁን በላይ ያላቸውን ዕይታ ጠይቋል።

የምጣኔ ሃብት ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ ባለፈው የበጀት ዓመት ቀርቦ ከነበረው 386.9 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ የቀረበው በጀት ከፍ ያለ ብልጫ ያለው ቢመስልም፤ በመገባደድ ላይ ያለው የበጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት መንግሥት 28 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ተጨማሪ በጀት ማስፀደቁን ጨምረው በማስታወስ አሁንም ጭማሪው የሚታይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ነገር ግን የቀጣይ ዓመት የአገሪቱ በጀት ከመጨመሩ ጎን ለጎን ይመዘገባል ተብሎ በገንዘብ ሚኒስትሩ የቀረበው የተጠባቂ ዕድገት ቁጥር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ ባለሞያዎቹ ጥያቄዎችን ያነሳሉ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ዙርያ ምጣኔ ሃብቶችን በሚገዳደርበት እና "በርካታ አገራት ዕድገታቸው የቁልቁል እንደሚሆን በተነበዩበት ወቅት፤ ከስምንት በመቶ የሚሻገር ዕድገትን መጠበቅ አስቸጋሪ ነው" ይላሉ አለማየሁ (ዶ/ር)።

"ምናልባት በገንዘብ ሚኒስትሩ የቀረበው የተጠባቂ ዕድገት መጠን በወረርሽኙ የሚደርሰውን ምጣኔ ሃብታዊ ጡጫ ያላካተተ ይሆን?" ሲሉም ይጠይቃሉ።

ወረርሽኙ በ2013 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት (ከቀጣዩ ሐምሌ እስከ መስከረም) ድረስ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ክፉኛ ይደቁሳል፤ ከዚያ ወዲያ ግን ተግ ይላል ብለን ብናስብ እንኳ ይላሉ ባለሞያው አለማየሁ "በእኔ ግምት ምጣኔ ሃብቱ በ5.6 በመቶ ይቀነሳል" ሲሉ የእራሳቸውን እይታ ያስቀምጣሉ።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ግምታቸውን ባደረጉት ጥናት ላይ መሠረት እንዳደረጉ ይገልፁና "ይህ ማለት የ8.5 በመቶ ዕድገት ላይ ለመድረስ ወረርሽኑ ከሚያደርሰው ጉዳት ጋር የሚደመር አጠቃላይ የ14 በመቶ ገደማ ይጠበቃል እንደማለት ነው" ይላሉ። ይህን መሰል ዕድገት ማስመዝገብ ደግሞ የመሆን ዕድሉ የጠበበ ነው ባይ ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ የተጠባቂ ዕድገት መግለጫ የወረርሽኙን ጉዳት ያላካተተ ከሆነ ግን ከጉዳቱ ጋር ተወራርዶ የሚኖረው ዕድገት 3 በመቶን የሚጠጋ ይሆናል እንደማለት ነው እንደእርሳቸው ግምት።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን እንደሚሉት ምንም እንኳ የወረርሽኙ ዳፋ ለኢትዮጵያ ባይቀርላትም፤ ቢያንስ እስካሁን እጅጉን የተጋነነ ስርጭትን ባለማስተዋሏ ወደሌሎች አገራት የምትልካቸው ቡናን የመሳሰሉ ምርቶች ፍላጎትም ሲቀንስ ባለመታየቱ መልካም ነገር ነው ይላሉ።

የኮሮናቫይረስ ጣጣ ለረጅም ጊዜ ሊዘልቅ እንደሚችል የሚሰጉት አለማየሁ (ዶ/ር) እንደሚሉት የወረርሽኙ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ላይ ብቻ ይቀጥላል ማለት "ይህ ጥሩ የሚባለው፥ ከቀናን (ቤስት ኬዝ ሲናርዮ) የሚባለው ግምት ነው" ይላሉ።

ወደ እውነታ የሚጠጋው ግምት ግን የወረርሽኙ ምጣኔ ሃብታዊ ጫና "አነሰ ቢባል ለስድስት ወራት ያህል፤ ያ ማለት እስከ ታኅሳስ ወር ድረስ" ይዘልቃል የሚለው ነው እንደ አለማየሁ (ዶ/ር)።

ለሁለት ሩብ የበጀት ዓመታት ያ ማለት እስከወርሃ ታህሳስ ድረስ የኮቪድ-19 መዘዝንና ቡጢውን ምጣኔ ሃብቱ ላይ ማሳረፉን ከቀጠለ ደግሞ ባለሙያው እንደሚገምቱት ምጣኔ ሃብቱ በአስራ አንድ በመቶ እንደሚቀንስ ነው።

"በታዳጊ አገራት ከፍ ያለ ዕድገትን ማስመዝገብ አስገራሚ ነገር አይደለም" የሚሉት አቶ ዋሲሁን፤ ከዚሁም አንፃር በአዲሱ የበጀት ዓመት 8.5 በመቶ ዕድገት ይመዘገባል መባሉ የሚደንቅ ሊሆን አይገባም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ከፍተኛ በጀት በጅተህ መሠረተ ልማት ላይ ማፍሰስ ብቻውን እኮ የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትን (ጂዲፒውን) እንዲያድግ ያደርገዋል" ሲሉ የእድገት ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉት ነገሮች መካከል ይጠቅሳሉ፤ አቶ ዋሲሁን።

አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ምጣኔ ሃብቱን ለማረጋጋት ብሎም ለማነቃቃት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ያደንቃሉ፤ የበለጠ እንዲያደርግም ይመክራሉ።

በአንድ በኩል መንግሥት እንደሌሎች በርካታ አገራት ምጣኔ ሃብቱን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት በኢትዮጵያ አውድ እንደማያዋጣ አውቆ እርሱን ያለማድረጉ እና ከዚያ ይልቅ ሥራዎች ከሞላ ጎደል እየተሰሩ ጥንቃቄዎች እንዲወሰዱ ማድረግን ዓይነተኛ አቅጣጫ አድርጎ መንቀሳቀሱ ተገቢ ነበር ይላሉ።

"ሰዎች የጤናቸው ሁኔታ ባሉበት መስሪያ ቤት አካባቢ እየተጠበቀ፤ ምጣኔ ሃብቱ እንዲንቀሳቀስ ማድረጉ ቆንጆ ነገር ነው።"

በሌላ ወገን ወረርሽኙ ለሚጎዱ ዘርፎች የማነቃቂያ ድጋፍ ማዘጋጀቱና ይህንን ለማቅረብ መስራቱም መልካም ነው ባይ ናቸው።

ሆኖም "የግል ክፍለ-ኢኮኖሚውን በተለይ ኢንደስትሪው አገልግሎት ላይ ያሉትን ሰዎች እንዴት እንደሚደግፍ ኮስተር ያለ ዕቅድ አውጥቶ መከታተል ያለበት ይመስለኛል። [የእስካሁኑን እንቅስቃሴ] ሳየው ወጥ የሆነ አሰራር አይመስልም" ይላሉ። "በደንብ ታስቦበት፣ በአጭር ጊዜ እንደዚህ [ይሆናል] በረጅም ጊዜ እንደዚህ [ይሆናል] ተብሎ እየተሄደበት አይመስለኝም።"

ከዚህም በዘለለ ቁጥራቸው ከሦስት ሚሊዮን ይሻገራል ያሏቸውን ራሳቸውን በራሳቸው (አንዳንዶቹ) ቤተሰባቸውን ጨምሮ የሚያስተዳድሩ ሰዎች "የመንግሥታዊ ድጋፍ ጠበል አልደረሳቸውም" ይላሉ።

የእነዚህ ሰዎች ዋነኛ ወጪ የመስሪያ ቦታ ኪራይ ክፍያ በመሆኑ እርሱን በተመለከተ በአከራዮች በጎ ፈቃድ ላይ የማይመሰረት የክፍያ ቅነሳ እርምጃ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

መንግሥት የኪራይ ወጪያቸውን በተወሰነ ድርሻ እንዲከፍል ማድረግም ሌላ የማነቃቂያ እርምጃ ሊሆን ይችላል ሲሉ አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚችለውን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ትንበያን በተመለከተ አቶ ዋሲሁን ግምታቸውን ሲያስቀምጡ "የተለጠጠ ታቅድና በጥረት የምትደርስበት ያህል ነው የምትሰራው። መንግሥት ይሄን ሲያስቀምጥ የጥረቱን ያስቀመጠ ይመስለኛል።"

"ምክንያቱም ምን ያህል በሽተኛ ይዘህ ነው 8.5 በመቶ አድጋለሁ የምትለው? ሰላሳ አርባ ሺህ ነው ወይንስ አሁን እየሆነ እንዳለው በየቀኑ መቶ መቶ እየጨመርን? የሚለውም መታየት አለበት" ሲሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቀጣይ ወራት ሊፈጥር የሚችለው እንቅፋት ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ይጠቅሳሉ።