በመሪዋ ድንገተኛ ሞት ግራ መጋባት ውስጥ ያለችው ቡሩንዲ

ፒየር ንኩሩንዚዛ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከሳምንታት በፊት በተደረገ ምርጫ ፓርቲያቸው ማሸነፉ የተነገረላቸው የቡሩንዲው ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ በድንገት ማለፍን ተከትሎ ማን ይተካቸዋል? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ በአገሪቱ ግራ መጋባት ተፈጥሯል።

ፕሬዝዳንቱ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ወርሃ ነሐሴ ላይ ስልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ ቢጠበቅም በሕገ መንግሥቱ መሰረት ለጊዜው የእሳቸውን ቦታ ሊተኩ የሚችሉት የፓርላማው አፈ ጉባኤ ናቸው።

ነገር ግን እስካሁን ድረስ አፈ ጉባኤው ቃለ መሐላ ያልፈጸሙ ሲሆን የፕሬዝዳንቱ መንበርም ያለተተኪ ባዶ ሆኖ የስልጣን ክፍተት ተፈጥሯል።

ካቢኔው ሐሙስ ዕለት ስብሰባውን ያደረገ ሲሆን ስብሰባውን የመሩት ከሁለቱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ተቀዳሚው ናቸው። በስብሰባውም በድንገት ያጋጠመውን የፕሬዝዳንቱን ሞት እንዴት እንደሚወጡት ተወያይተዋል።

በአገሪቱ በተፈጠረው የስልጣን ክፍተት ምክንያት በገዢው ፓርቲ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፤ ከገዢው ፓርቲ ምክትሉ ኢቫሪስት ንዳዪሺምዬ እና የፓርላማው አፈ ጉባኤ ፓስካል ንያቤንዳ ዋነኛ ተፋላሚዎቹ ናቸው ተብሏል።

ባሳለፍነው ጥር ወር ሁለቱም በገዢው ፓርቲ በኩል ፕሬዝዳንታዊ እጩ ለመሆኑ ሲዘጋጁ እንደነበርም ተገልጿል።

የምስሉ መግለጫ,

ባለፉት 20 ዓመታት በስልጣን ላይ ሳሉ ህይወታቸው ያለፈ አፍሪካ አገራት/ግዛት መሪዎች

የቡሩንዲ መንግሥት ቃል አቀባይ ፕሮስፐር ንታሆዋሚዬ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ አሁን ያለው ሁኔታ በፍርድ ቤት ይፈታል ብለዋል።

"ከሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ ጋር እየተመካከርን ነው። አሁን ያለውን የስልጣን ክፍተት እያጠናው ነው። ነገር ግን ጥቂት ቀናትን ሊወስድ ይችላል'' ብለዋል።

በሌላ በኩል የፕሬዝዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ሞት ጉዳይ አሁንም በርካታ መላ ምቶችን እያስተናገደ ነው። በርካቶች ፕሬዝዳንቱ የሞቱት በኮሮናቫይረስ ነው ቢሉም መንግሥት መጀመሪያ ላይ እንዳለው በልብ ሕመም መሞታቸውን አጠንክሮ እየገለጸ ነው።

የፕሬዝዳንቱን ሞት ተከትሎ በታወጀው የሰባት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ወቅት ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ ከመንፈሳዊ ዝማሬዎች ውጪ ሌሎች ሙዚቃዎች እንዳይከፈቱ የአገሪቱ ካቢኔ ወስኗል።

ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ሬዲዮ ጣቢያዎች የፕሬዝዳንቱ ሞት ከተነገረበት ዕለት አንስቶ መንፈሳዊ ዝማሬዎችን ብቻ ነው እያሰሙ ያሉት።