ሰዎችን በፊት ገጽታቸው "ጉግል" ማድረግ ሊጀመር ነው

ፒምአይስ

የፎቶው ባለመብት, PIMEYES

የምንፈልገውን ሰው ስሙን ጽፈን በበይነ መረብ ብንፈልገው እናገኘዋለን። ያም ካልሆነ በአድራሻው፣ ያም ካልሆነ በስልክ ቁጥሩ።

አሁን እየመጣ ያለው ቴክኖሎጂ ግን ሰዎችን በፊት መልካቸው ፈልፍሎ የሚያወጣ ሆኗል።

ይህ ፒምአይስ የሚባል ነገር አንድ ሰው ራሱንም ሆነ የሌላ ሰው ፎቶ በማስገባት በይነ መረብ ተጨማሪ ምስሎችን ለቅሞ እንዲያመጣ የሚያደርግ ነው።

ይህ ነገር ታዲያ የሰዎችን ምስጢርና የግላዊ መብት የሚጥስ ነው በሚል ተቃውሞ እየቀረበበት ነው።

ፒምአይስ ግን ራሱን የሚገልጸው በዚህ መንገድ አይደለም። ሰዎች እንዲያውም ምስላቸው የት እንዳለ እንዲደርሱበት አግዣቸዋለሁ ይላል።

"ቢግ ብራዘር ዋች" የተባለ በሰዎች ምስጢር ጥበቃ ላይ የተሰማራ ድርጅት የእዚህ ቴክኖሎጂ መፈጠር አገራት ዜጎቻቸውን በቀላሉ እንዲሰልሉ ያስችላቸዋል። ይህ ደግሞ ጥሩ ዜና አይደለም።

ከዚህም ባሻገር ኩባንያዎች ሰዎችንና ምስላቸውን እንዲነግዱበት ይገፋፋቸዋል ይላል ቢግ ብራዘርስ።

የፊት ገጽታ የበይነ መረብ አሰሳ የሰዎችን ግላዊ መብት የሚጋፋና እጅግ አደገኛ ውጤት እንዲሚኖረው ቢግ ራዘርስ ዋች ያሳስባል።

አማዞን ከዚሁ ቴክኖሎጂ ጋር የሚቀራረብ ፊትን የሚለይ መሣሪያ ተግባር ላይ አውሎ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ይህን ተግባሩን ከሰሞኑ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ አቁሞታል።

ይህ ፒምአይስ የተባለው ድረ ገጽ በፖላንድ አገር የተቋቋመ ሲሆን ሥራውን የጀመረው ከሦስት ዓመት በፊት በ2017 ነው። አጀማመሩ እንዲሁ እንደ ትርፍ ጊዜ ማሳለፍያ ሆኖ ወደ ንግድ ድርጅትነት የተቀየረው ባለፈው ዓመት ነበር።

አሁን ከ6ሺህ በላይ አባላትና ተጠቃሚዎች አሉት።

ይህ ደረ ገጽ ደንበኞቹ የፈለጉትን ፎቶ በነጻ እንዲለጥፉ ያበረታታል። የለጠፉትን ምስል ከግምት ውስጥ በማስገባት ያን ፎቶ የሚመስሉ ሰዎችን፣ ከጡመራ ገጾች፣ ከፌስቡክና ከሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጭምር ለቃቅሞ ያመጣል።

የቢግ ብራዘር ዋች ዳይሬክተር ሲልኪ ካርሎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የዚህ ፎቶን የመበርበር ቴክኖሎጂ በሥራ ላይ መዋል አስደንጋጭ ነገር ነው። ሰዎችን ያለ ፈቃዳቸው የመከታተልና ሴቶችና ሕጻናትንም ለወሲብ ቀበኞች አሳልፎ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ፒም አይስ ለዚህ ስጋት በሰጠው ምላሽ፣ የእኛ አገልግሎት ለጥፋት እንዲውል አንፈልግም፤ ኾኖም ግን ማንኛውም ቴክኖሎጂ ለጥሩም ለበጎም ሊውል እንደሚችል መዘንጋት የለበትም ብሏል።

ድርጅቱ የሰዎችን ፎቶ ከፌስቡክ ገጻቸው እንደማይሰርቅ ቢናገርም ቢቢሲ በጋዜጠኞቹ ፎቶዎች ላይ ባደረገው የሙከራ ፍለጋ ፒም አይስ ይህን እንደሚያደርግ ደርሶበታል።

ፒምአይስ ግን ያስተባብላል፣ ምናልባት ፎቶዎቹ ከፌስቡክ ተወስደው ሌሎች ድረገጾች ላይ ውለው ሊሆን ይችላል፤ እኛ ፎቶ የምንወስደው ይህንን እንደናደርግ ከፈቀዱ ድረገጾች ብቻ ነው ብሏል።

የሰው ገጽታን የመለየት ሥራ ውስጥ የተሰማራው ክሊርቪዊኤአይ 6 ቢሊዮን ፎቶዎችን በቋቱ ውስጥ ማስገባቱ በቅርብ ጊዜ ውዝግብ መፍጠሩ ይታወሳል። ይህን ያደረገው የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)ን ጨምሮ 600 መቶ የሚሆኑ የስለላ ድርጅቶች ወንጀለኞችን ለማደን እንዲጠቀሙበት በሚል ነው።

ድርጅቱ ይህን ያደረገው የግለሰቦችን ፍቃድ ሳያገኝ ከዩቲዩብ፣ ከፌስቡክና ከትዊተር ገጾችም ነበር።

እነዚህ ድርጅቶችም ከሊርቪውኤአይ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ጠይቀው ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች ልክ እንደ ጣት አሻራ ሁሉ ፊታቸውን የሚለዩ መሣሪያዎች እየተፈጠሩና አገልግሎት ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። እነዚህ መሣሪያዎች ግን የጥቁሮችን የፊት ገጽታ ለመለየት እየተቸገሩ ነው።

ከዚህ በኋላ የሚኖረው ዓለም ምናልባት ሰዎች የግሌ ወይም ምስጢሬ ብለው ሊያስቀምጡት የሚችሉት ምንም ዓይነት ሰነድ እንዳይኖር የሚያደርግ ሊሆን ይችላል ብለው የሚሰጉ በርካቶች ናቸው።

የሁሉም ሰዎች ምስጢር የአደባባይ ምስጢር የሚሆንበት ዘመን እየመጣ ያለ ይመስላል።