እናትና ልጅ የህክምና ባለሙያዎች በአሜሪካ ታሪክ ሰሩ

እናት ሲንቲያ ኩጂ እና ልጇ ጃስሚን
የምስሉ መግለጫ,

እናት ሲንቲያ ኩጂ እና ልጇ ጃስሚን

የትውልድ መሰረታቸው ጋና ውስጥ የሆነው እናትና ልጅ በተመሳሳይ ጊዜ በአንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ህክምና ተምረው በመመረቅና በአንድ ሆስፒታል ውስጥ በመስራት የመጀመሪያዎቹ በመሆን በአሜሪካ ታሪክ አስመዘገቡ።

እናትና ሴት ልጃቸው አሜሪካ ውስጥ በሊዊዚያና ግዛት ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሚገኝ የህክምና ትምህርት ቤት አንድ ላይ በመማር ተመርቀው እዚያው በሚገኝ ሆስፒታል ሥራ መጀመራቸው የመጀመሪያ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ተነግሯል።

እናት ሲንቲያ ኩጂ በጋናዋ ኬንያሲ ከተማ ውስጥ ተወልዳ ወደ አሜሪካ የሄደች ሲሆን ከልጇ ጃስሚን ጋር በአንድ የህክምና ትምህርት ቤት ተምራ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተመርቀው ሥራ የጀመሩት አንድ ላይ ነው።

እናትና ልጅ ሥራ በጀመሩበት ሆስፒታል ውስጥ የወቅቱ የዓለማችን አሳሳቢ የጤና ችግር በሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ህሙማንን ለማከም ከፊት መስመር ከተሰለፉ የጤና ባለሙያዎች መካከል በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

እናት ሲንቲያ እንዳለችው ከልጇ ጋር በአንድ ላይ መስራት "የህልም ዕውን የመሆን ያህል ነው" ስትል የተፈጠረባትን ደስታ ገልጻለች።

ልጅ ጃስሚን ስለእናቷና ስለእራሷ በቢቢሲ ተጠይቃ እንደተናገረችው፤ የሁለታችን ስኬትና ልምድ ለሌሎች መልካም ምሳሌና መነቃቃት እንደሚሆን ተስፋ እንዳለት ተናግራለች።

"ከእናቴ ጋር በዚህ መንገድ አብሬያት በመጓዝ ሌሎች ሴቶችንና ጥቁሮች ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ መነቃቃት በውስጣቸው ለመፍጠር ምክንያት ስለሚሆን ኩራት እንዲሰማኝ ያደርገኛል" ብላለች።

ጨምራም ከትምህርት ጀምሮ በሥራው ዓለምም ከእናቷ ጋር በመሆኗ ደስተኝነት እንደተፈጠረባት "የጀመርነውን ጉዞ አብረን በመቀጠላችን በጣም ደስተኛ ነኝ" በማለት ገልጻዋለች።

አፍሪካ አሜሪካዊያኑ እናትና ልጅ በአንድ የህክምና ትምህርት ቤት አብረው ከተማሩ በኋላ በአንድ የህክምና ተቋም መስራታቸው ከፍተኛ አድናቆትን ፈጥሯል።