ብልጽግናና ህወሓት ስላልተስማሙ ምርጫ ቦርድ ኦዲተሮች ሾመ

የፎቶው ባለመብት, NEBE
የአራት ድርጅቶች ጥምረት የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ንብረት ክፍፍልን በተመለከተ በብልጽግናና በህወሓት መካከል ከስምምነት ላይ ስላልተደረሰ ምርጫ ቦርድ ሁለት ኦዲተሮችን መሾሙን አስታወቀ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳመለከተው የኢህአዴግ የመፍረስ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ብልጽግናና ህወሓት የሚስማሙበት አንድ የጋራ አጣሪ እንዲመርጡ ለማስቻል የተደረገው ጥረት አልተሳካም ብሏል።
ስለሆነም ቦርዱ ብልጽግና ፓርቲ እና ህወሓት በየበኩላቸው የመረጧቸው አንድ አንድ የሒሳብ አጣሪዎች በጋራ በመሆን የንብረት ማጣራት ሥራውን እንዲያከናውኑ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህም ውሳኔ መሰረት የንብረት ማጣራቱ ሥራውን እንዲያካሂዱ የተመረጡት ድርጅቶች እነማን እንደሆኑ ቦርዱ ያልገለጸ ቢሆንም፤ ነገር ግን ሥራቸውን በጋራ የሚያከናውኑበትን ዝርዝር ጉዳዮችን በማዘጋጀት ለቦርዱ እንሚያቀርቡ ተገልጿል።
ከ25 ዓመታት በላይ አገሪቱን ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ከከሰመ በኋላ የአማራ ዴሞክረሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ብልጽግና የተሰኘውን ፓርቲ ሲመሰረትቱ ህወሓት እራሱን ከአዲሱ ፓርቲ ማግለሉ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኢሕአዴግ እንዲፈርስና የሦስቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ወራሽ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በስድስት ወር ውስጥ የንብረት ክፍፍላቸውን አጠናቀው እንዲያቀርቡ ወስኖ ነበር።
በዚህም መሰረት ብልፅግና ከግንባሩ ሃብት ሦስት አራተኛውን እንዲሁም ህወሓት ደግሞ አንድ አራተኛውን እንዲወስዱ ቦርዱ ቢወስንም፤ የብልጽግና ፓርቲ የንብረት ክፍፍሉ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል በነበረው የአባላት ብዛት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል የሚል አቤቱታ ማቅረቡን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ነገር ግን ቦርዱ የሃብት ክፍፍሉ የፓርቲው ሕገ ደንብ "ሁሉም ፓርቲዎች በግንባሩ የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው" በማለት ያስቀመጠውን መሰረት በማድረግ መወሰኑን ገልጾ "ሆኖም ብልጽግና ከዚህ የተለየ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ማስረጃ ወይም ሰነድ ካለው ለአጣሪው ማቅረብ እንደሚችል" ምላሽ መሰጠቱን አመልክቷል።
ከኢህአዴህ መክሰም በኋላ ተመሰረተው ብልጽግና ፓርቲ ከሦስቱ የቀድሞ ገዢ ፓርቲ አባላት በተጨማሪ የቀድሞ አጋር ድርጅቶችን በአባልነት በማካተት የተመሰረተ አገር አቀፍ ፓርቲ ነው።