የኮሮናቫይረስ ውጤት መዘግየት ስጋት እየፈጠረ ነው

ምርመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአስከሬን ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ በስፋት እየተካሄደ ነው። ቀደም ሲል በተለየ ምክንያት ካልተፈለገ በስተቀር ምርመራው አይካሄድም ነበር።

ምርመራው የቫይረሱን የስርጭት መጠን ለማወቅ ይረዳል። ሌሎችም ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያግዝ ነው።

ከበሽታው እየተስፋፋ ከመምጣት አንጻር የምርመራው ውጤት ከመዘግየት ጋር ተያይዞ ችግሮች እየተከሰቱ ነው።

ሁለቱን እንመልከት።

አዲስ አበባ፣ ልደታ ክፍለ ከተማ

ቢኒያም አሸናፊ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አብነት አካባቢ ነዋሪ ነው።

ከሳምንታት በፊት በሰፈሩ የተፈጠረውን መቼም አይረሳውም።

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አንዲት ግለሰብ በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው ያልፋል።

"እኛ አካባቢ የተፈጠረው ነገር ህክምና ላይ የነበሩ የሰፈራችን ነዋሪ ሴት ውጤታቸው ሳይታወቅ በመሞታቸው አስከሬናቸው ለቤተሰብ ተሰጠ። በአጋጣሚም ውጤቱ የታወቀው አስከሬን ከወጣ በኋላ ነበር" ሲል ቢኒያም ያስታውሳል።

ግለሰቧ የህይወታቸው አልፎ ግብዓተ መሬታቸው ከተፈጸመ በኋላ ውጤታቸው ታወቀ። የኮሮናቫይረስ እንደነበረባቸው ተረጋገጠ።

ይህም በአካባቢው ብዙ መዘዝ ይዞ ነበር የመጣው።

"ብዙ ንኪኪዎች ነበሩ። በአኗኗራችን ምክንያት ድንኳን ውስጥ ለለቅሶ የተቀመጠ ሰው ስለነበረ በጣም ብዙ ሰው ነው በቫይረሱ የተያዘው። በቁጥር ደረጃ ይህ ያህል ነው ማለት ባልችልም። ነገር ግን በንክኪ የተነሳ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቂ ነበሩ።"

በኮሮናቫይረስ ምርመራው ውጤት መዘግየት፣ የአካባቢው ነዋሪ የተጠጋጋ አኗኗር ስላለው እና በለቅሶ ሥነ-ሥርዓት ወቅት በነበረው ንክኪ ምክንያት ብዙዎች ቫይረሱ እንዲይዛቸው ዕድል ፈጥሯል።

የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ከቫይረሱ በኅብረተሰቡ ውስጥ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አንዳንድ አካባቢዎችን ከእንቅስቃሴ ሊዘጋ እንደሚችል በዚያው ሰሞን አስታውቆ ነበር።

የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ነዋሪዎች ግን በወጣቶች አስተባባሪነት አካባቢውን ለሁለት ሳምንት ከእንቅስቃሴ ውጪ ለማድረግ በመወሰን ቀድመው ተገበሩት።

"የተዘጋበት ምክንያት መንደር ውስጥ ቁጥሩ እየበዛብን ሲሄድ እዚው ያለን ወጣቶች በጎ ፈቃደኞች ሌላው አካባቢ እና ማኅበረሰብ እንዳይጠቃ በማሰብ ከጤና ባለሙያዎችና እና ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋጋር ራሳችንን ነው ኳራንቲን ያደረግነው" ብሏል ቢኒያም።

በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችም የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው የሁለት ሳምንቱን ጊዜ አጠናቀው አሁን ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል።

ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ደረጃ በቫይረሱ ስርጭት ቀዳሚ የነበረው ልደታ ክፍለከተማ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ

ወይዘሮ ጸዳለ ሰሙንጉሥ የሰሜን ሰዋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኃላፊ ናቸው።

የዚህም ታሪክ መነሻ አዲስ አበባ። ሸገር ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ወድቀው ወደ ግል ሆስፒታል ለህክምና ያቀናሉ።

በህክምና ወቅትም የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይደረግላቸዋል። ውጤቱ ይፋ ከመሆኑ በፊት ግን ህይወታቸው ያልፋል።

"የአስከሬን ምርመራ ውጤቱ ቶሎ አልደረሰም ነበር። ቤተሰብ አና ወዳጅ ዘመድ አስከሬን ተቀብሎ ወደ ትውልድ ቀዬው እንሳሮ ያቀናል። በዚያም ሥረዓተ ቀብሩ ሲካሄድ በርካታ ሰው ተገኝቶ ነበር። ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተካሂዷል" ይላሉ ወይዘሮ ጸዳለ።

የህክምና ማዕከሉ ውጤቱ የደረሰው የግለሰቡ አስከሬን ከአዲስ አበባ ውጪ ተጓጉዞ አንደባህሉ ሰው ተሰብስቦ ግብዓተ መሬት ከተፈጸመ በኋላ ነበር። ውጤቱም ሟች የኮሮናቫይረስ ህመምተኛ እንደነበሩ የሚያረዳ ነበር።

ከዚያም መልዕክት ለአካባቢው የጤና ኃላፊዎች ደረሰን። ሟች ኮሮናቫይረስ ስለነበረበት አስፈላጊው የበሽታ አሰሳና ንኪኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየት አስፈላጊው ሥራ እንዲከናወን ትዕዛዝ ተላለፈ።

ወ/ሮ ጸዳለ እንደሚሉት "ከእንሳሮ ወረዳ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ርብርብ አድርገን 53 የሚሆኑ ሰዎችን የመለየት እና ቀደም ተብሎ ወደተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አደረግን። ተጨማሪ 20 ሰዎች ደግሞ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ወደሚገኘው ለይቶ ማቆያ ገብተዋል።"

ወደ ለይቶ ማቆያው እንዲገቡ የተደረጉት ሰዎች አብዛኛዎቹ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኙ ናቸው። ውጤቱ ቀደም ተብሎ ቢታወቅ ኖሮ ይህ ሁሉ ሰው ተጋላጭ እንደማይሆን ባለሙያዎቹ ያምናሉ።

"የቅርብ ቤተሰቦቹን ስናስገባ ከእሱ ጋር ማን ተገናኝቷል የሚለውን ነገር እየለየን ነው። የለየናቸው ከአስከሬኑ ጋር ንኪኪ የነበራቸው እና በቀብሩ ላይ የነበሩ ናቸው" ምክትል ኃላፊዋ።

ወይዘሮ ጸዳለ እንደሚሉት የምርመራ ውጤት መዘግየት የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ላይ የእራሱ ተጽእኖ አለው።

"የላቦራቶሪ ውጤት በአንድ ቀን መድረስ ካልቻለ መዘግየት ኖሮ ሁለት እና ሦስት ቀን የሚቆይ ከሆነ በዚያ መካከል ብዙ ንክኪ ሊፈጠር ይችላል። የተመረመረ ሰው ውጤት እስኪታወቅ በተለየ ቦታ ማቆየት ቢቻል ለሌላ ሰው የማስተላለፍ ዕድሉ ይቀንሳል" ይላሉ።

በአካባቢው የውጤት መዘግየት ሲከሰት ግን ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ቀደም ሲልም ከቫይረሱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሁለት ሰዎች አዲስ አበባ ናሙና ሰጥተው ውጤታቸውን ሳያውቁ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን አቅንተው ነበር።

ዘግይቶም ቢሆን በደረሰው ውጤት የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

"ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተገናኝተዋል። አንደኛው ከቤተሰቦቹ ጋር እያለ ነው ተደውሎ ውጤት የተነገረው። እንግዲህ በሽታውን ወደ ቤተሰቦቻቸው የማስተላለፍ ዕድል አላቸው" ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህም ምርመራው የሚደረግላቸው ሰዎች ንክኪ ያላቸው ወይም ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ በመሆናቸው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ባሉበት እንዲቆዩ ማድረግን እንደ አንድ መፍትሄ ያቀርባሉ ወ/ሮ ጸዳለ።

በአስከሬን ላይ የሚደረገው ምርመራም ናሙና ተወስዶ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ አስከሬን ካልተሰጠ በተለያዩ አጋጣሚዎችና በቀብር ሥነ ሥርዓት ጊዜ በሚደረግ ንክኪ ቫይረሱ ወደ በርካታ ሰዎች እንዳይሻገር በማድረግ የወረርሽኙን መስፋፋት መቀነስ ይችላል ይላሉ።

ወይዘሮ ጸዳለ ካላቸው ልምድ በመነሳት የመርመሪያ ማሽኑ ናሙና ማዘጋጀትን ጨምሮ ናሙናውን ለመመርመር የሚፈጀመውን ጊዜ አካቶ የአንድ ሰውን ውጤት በአንድ ቀን ማደረስ እንደሚቻል ይናገራሉ።

ለዚህም ነው "ቢዘገይ ቢዘገይ በአንድ ቀን ውጤት መነገር ግዴታ መሆን አለበት" የሚሉት።

የበሽታውን ምልክት አላሳዩም ብሎ ናሙና የሰጡ ሰዎችን ወደ ፈለጉበት እንዲሄዱ መልቀቅ የአቅም ጉዳይ ይመስለኛል የሚሉት ምክትል ኃላፊዋ ውጤቱ በቶሎ እንዲታወቅ ከተደረጋ በዚህ በኩል ያለውን ችግር መቅረፍ ይቻላል ይላሉ።

"ወደ ቀያቸው የሄዱት ሁለቱ ሰዎች ከታወቀ ሰው ጋር ግንኙነት ነበራቸው። እነሱም ከብዙ ሰው ጋር ግንኙነት ነበራቸው። ውጤቱ ባይዘገይ የመከላከል ሥራ ለመስራት ዕድል ይፈጥርልናል" ሲሉም ያስረዳሉ።

የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ከሄደ አይደለም የተመረመሩ ሰዎች ቫይረሱ ኖሮባቸው ምልክት ያላሳዩትም በቤታቸው ሆነው ራሳቸውን በማግለል እስኪድኑ እንዲቀመጡ ሊደረግ ይችላል ይላሉ። በምሳሌነት ደግሞ ቫይረሱ በተስፋፋባቸው ያደጉት ሃገራት ተመሳሳይ ነገር እየተካሄደ መሆኑን ይገልጻሉ።

ኅብረተሰቡም በምንም ምክንያት ይሁን ተመርምሮ ውጤቱ እስኪታወቅ ራሱን ለይቶ በመቀመጥ ውጤቱን በመጠበቅ ቤተሰብንም ሆነ ሌሎችን ከቫይረሱ ለመታደግ ወሳኝ ነገር እርምጃ ነው ይላሉ።

በኮሮናቫይረስ ምርመራ ውጤት መዘግት ዙሪያ የጤና ጥበቃ ሚንስቴርንና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ሃሳብ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።