ኮሮናቫይረስ፡ የእንቅስቃሴ ገደብና የታዳጊዎች የአእምሮ ጤና

የሚጫወቱ ልጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር በማሰብ ይጠቅመናል ያሉትን እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ። የሰዎች እንቅስቃሴን በመገደብ ንክኪ እንዲቀንሱ ማድረግ ደግሞ የመጀመሪያው ነው።

ታዲያ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በአካል ማግኘት አስቸጋሪ ሲቀርና ሃሳብ ጭንቀታቸውን አይን አይናቸውን እያዩ ማካፈል ሳይችሉ ሲቀሩ ደግሞ ቀላል የማይባል ሥነ ልቦናዊ ጫና ይደርስባቸዋል።

በተለይ ደግሞ በአስራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ታዳጊዎች ላይ ጫናው ይበረታል እተባለ ነው።

በእንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ወቅት የታዳጊዎች የአንጎል እድገት፣ አጠቃላይ ባህሪ እና የአእምሮ ጤና ሊስተጓጎሉ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

ምናልባት ቀላል የማይባል ጊዜያቸውን ማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ተጠምደው ማሳለፋቸው ድብርት ውስጥ እንዳይገቡ የሚያደርጋቸው ሊመስል ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን እንዲያውም በርካታ ሰዓታትን ማኅራዊ ሚዲያዎች ላይ አፍጥጦ መዋል ከባድ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ያስከትላል።

ለዚህም ይመስላል በርካታ አገራት የእንቅስቀሴ ገደቡን ላላ በማድረግ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ቅድሚያ እየሰጡ የሚገኙት።

እንደባለሙያዎቹ ጉርምስና የሚባለው ዕድሜ ከ10 እስከ 24 ዓመት ያሉትን ታዳጊዎች የሚያካትት ሲሆን በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ልጆች ለብዙ ነገሮች ተጋላጭ እንደሚሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብዙ ጊዜ ደግሞ እነዚህ ታዳጊዎች በዚህ የእድሜ ክልላቸው ውስጥ ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸውን ቅርበት የሚቀንሱበትና ከሚመስሏቸው ጓደኞቻቸው ጋር ከምንጊዜውም በበለጠ የሚቆራኙበት ወቅት ነው።

ይህ በተፈጥሮ የሚመጣ ባህሪ ታዳጊዎቹ ወደ ጉልምስና ለሚያደርጉት ጉዞና ለአንጎላቸው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪም ይህ ጊዜ በቀላሉ የአእምሮ በሽታዎች የሚያጋጥሙበት ወቅትም ሊሆን እንደሚችልም ይታወቃል ይላሉ ባለሙያዎቹ።

የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ ከባድ ያደርጋቸዋል የሚሉት በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሳራ ጄን ብላክሞር ናቸው።

"የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው ዓለም የሚገኙ ታዳጊዎች ከምን ጊዜውም በበለጠ ጓደኞቻቸውን ማግኘት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ነገሮችን ከባድ ሆኖባቸዋል። ወሳኝ በሚባለው የእድገት ደረጃቸው ላይ ሲደርሱ ጓደኞቻቸውን በአካል ማግኘት አለቻላቸው አጠቃላይ እድገታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል።’’

"ምንም እንኳን የአካላዊ ርቀት ሕጎቹ ጊዜያዊ ቢሆኑም፤ ይህ ከጓደኛ ጋር የመገናኘት ዕድልን ከአንድ ታዳጊ ሕይወት ላይ ለአራትና ለአምስት ወራት ሲወሰድበት እድገት ላይ የሚኖረው ጫና ቀላል አይደለም" ሲሉ ፕሮፌሰር ሳራ ይናገራሉ።

ስለዚህም በኮሮናቫይተረስ ወረርሽኝ ምክንያት ልጆች በቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸው የእራሱ የሆነ ሥነ ልቦናዊ ጫና ይኖረዋል። ቢሆንም ግን ይህ ከማኅበራዊ ግንኙነት የመገለሉ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ እንደማይሆን ተስፋ ያደርጋሉ።