በዛፍ ላይ ተሰቅለው የተገኙት ጥቁር አሜሪካውያን አሟሟት ላይ ዳግም ምርመራ ሊጀመር ነው

ለሮበርት ፉለር ፍትህ የሚል ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ፌደራል ባለስልጣናት በቅርቡ በዛፍ ላይ ተንጠልጥለው የተገኙት ሁለት ጥቁር አሜሪካውያን አሟሟት ላይ የተደረገውን ምርመራ ሊገመገም እንደሆነ አስታውቀዋል።

ግለሰቦቹ ሞተው የተገኙት በካሊፎርኒያ ሲሆን፤ ከአሟሟታቸውም ጋር በተያያዘ የተቀጣጠለውንም ተቃውሞ ተከትሎ ነው ምርመራው እንደገና እንዲጀመር የተወሰነው።

የአካባቢው ፖሊስ ሮበርት ፉለርና ማልኮልም ሃርሽ የተባሉት ጥቁር አሜሪካውያን ግድያ አይደለም ብሏል።

በካሊፎኒያ ግዛት በተለያየ ከተማ በዛፍ ላይ ተንጠልጥለው የተገኙት ጥቁር አሜሪካውያኑ በሁለት ሳምንታት ልዩነት ነው የሞቱት።

ብዙዎች ራሳቸውን አጥፍተው ሳይሆን ተገድለው ነው በሚልም ምርመራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

የ24 አመቱ ሮበርት ፉለር ፓልሜድ በምትባለው አካባቢ ከሚገኝ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ የተገኘው ሰኔ 3፣ 2012 ዓ.ም ነው።

ምንም እንኳን የአካባቢው ባለስልጣናት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ራሱን አጥፍቶ ነው ቢሉም፤ ብዙዎች አልተቀበሉትም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ምርመራ እንዲካሄድ ፊርማቸውን አሰባስበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቤተሰቦቹም ቢሆኑ ራሱን ነው የገደለው የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ሊዋጥላቸው አልቻለም

"የሚነግሩን ነገር በሙሉ ስህተት ነው፤ በምንም መንገድ ተቀባይነት የለውም። ወንድሜ ራሱን ማጥፋት አይፈልግም ነበር" በማለት የሮበርት ፉለር እህት ዳይመንድ አሌክሳንደር ተናግራለች።

ሌላኛው ሟች ማልኮልም ሃርሽም ግንቦት 23፣ 2012 ዓ.ም ቪክቶርቪል በምትባል አካባቢ በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ነው የተገኘው።

ባለስልጣናቱም የ37 አመቱ ማልኮልም ራሱን አጥፍቷል የሚል ግምት ቢኖራቸውም አሟሟቱን በተመለከተ ይፋዊ መረጃ ገና አልወጣም።

"አሟሟቱን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች አሉን፤ ምላሾችም እየጠበቅን ነው። ወንድሜ ሁሉን ወዳጅ ነበር። ለቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን ለሁሉ ቀና ነበር። እንዲህ አይነት ሰው ራሱን ያጠፋል ማለት አያሳምንም" በማለት አህቱ ሃርሞኒ ሃርሽ ለሚዲያዎች ተናግራለች።

የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የካሊፎርኒያ ግዛት ምርመራ ቢሮ፣ የአሜሪካ የሲቪል መብቶች የፍትህ ዘርፍ ክፍል ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በላኩት መመግለጫ ግለሰቦቹ ላይ የተከናወኑትን ምርመራዎች እየተገመገሙና እንደገናም ምርመራ ሊጀመር መሆኑን ነው።

የመጀመሪያ ምርመራው የተከናወነው በሎስ አንጀለስና ሳንበርናርዲኖ ፖሊስ ቢሮዎች ሲሆን ለግምገማውም እንደሚተባበሩ አስታውቀዋል።

የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ የሁለቱ ግለሰቦች አሟሟት ላይም ምርመራ እንዲካሄድ ጫና አሳርፏል።