"ሙሶሎኒ በኢትዮጵያ የመርዝ ጋዝ አልተጠቀመም" ያለው ጋዜጠኛ ሐውልት እንዲፈርስ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

ኢንድሮ ሞንታኔሊ ሐውልት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤርትራዊቷን በባርነት ገዝቶ የኖረው እና "ሙሶሎኒ በኢትዮጵያ የመርዝ ጋዝ አልተጠቀመም" ያለው ጋዜጠኛ ሐውልት እንዲፈርስ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

ኢንድሮ ሞንታኔሊ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ነበር። የዚህ ሰው ችግር ቅኝ ግዛት እጅግ አስፈላጊም ተገቢም ነበር ብሎ ማመኑ ነው።

ሰሞኑን በዚህ ሰውዬ ላይ ቂም የያዙ ሰዎች ለእርሱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የቆመን ሐውልት በቀለም ፊቱን አበለሻሽተውታል። "አንተ ሴት ደፋሪ፣ አንተ ዘረኛ" ብለውም በሚላን ከተማ የቆመውን ሐውልቱን በቀለም ቸክችከውበታል።

የጣሊያን ፖሊስ ይህን ደርጊት ማን ነው የፈጸመው ብሎ ሲጠይቅ ጸረ ዘረኝነትን ያነገቡ ሰልፈኞች "እኛ ነን ሐውልቱን ያበላሸነው" ብለዋል።

ይህ ሐውልት ቆሞ የሚገኘው በጣሊያን ሚላን ፓርክ ውስጥ ነው።

ተቃዋሚዎች ይህ ሐውልት በአስቸኳይ መፍረስ አለበት ብለው ተነስተዋል።

ሞንታኔሊ የሞተው እንደ አውሮፓዊያኑ በ2001 ነበር።

እአአ በ1930ዎቹ በውትድርና አገልግሎት ላይ ሳለ አንዲት የ12 ዓመት ኤርትራዊትን በገንዘብ ገዝቶ እና በኋላም አግብቷት ይኖር እንደነበር አምኗል።

በአሜሪካና በአውሮፓ ጸረ ባርነትና ጸረ ዘረኝነት ተቃውሞዎች መስፋፋታቸውን ተከትሎ በጣሊያንም ተቃዋሚዎች የዚህን ሰው ሐውልት በአስቸኳይ አፍርሱልን እያሉ ነው።

ይህ ዓለም አቀፍ መልክ እየያዘ የመጣው የጸረ ዘረኝነትና የጸረ ባርነት ተቃውሞ እየተስፋፋ የመጣው ባለፈው ወር በሜኔሶታ ግዛት ሚኒያፖሊስ ከተማ አንድ ነጭ ፖሊስ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊያን መተንፈስ እስኪሳነው ድረስ በጉልበቱ ማጃራቱን አንቆ በግፍ ከገደለው በኋላ ነበር።

በጣሊያን አገር ሬተስቱደንቲሚሊኖ የሚባሉ የመብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ይህንን ሞንታኔሊ የተባለ ሰው "እጅግ ነውረኛና ዘረኛ የነበረ፣ የቅኝ ግዛት ደጋፊና የባርነት አቃፊ›› ሲሉ ይነቅፉታል።

"ለዚህ ነውረኛ ሰው ሐውልት ማቆም ነውር ነው" ሲሉ ቅዋሚያቸውን አስተጋብተዋል።

የሚላን ከንቲባ በበኩላቸው "ሞንታኔሊ ሐውልቱ የቆመለት በነበረው የጋዜጠኝነት ጀብዱ ነው" ሲሉ ተከላክለውታል።

"እንዴት ያለ ጋዜጠኛ ነበር መሰላችሁ፤ ለነጻ ፕሬስና የመናገር ነጻነት ሲታገል ነው የኖረው። እያንዳንዳችን ስለ ሕይወታችን መለስ ብለን ብናይ ከሐጥያት ነጻ ነን ወይ? የአንድ ዜጋ ሕይወት መለካት ያለበት ከጥላሸቱ ጭምር ነው" ሲሉ ሰውየውን ተከላክለውለታል፤ ከንቲባው።

ትናንትና እሑድ የሚላን ማዘጋጃ ቤት የጽዳት ሠራተኞች ተቃዋሚዎች ያጎደፉትን የሰውየውን ሐውልት ሲያጸዱ ነው የዋሉት።

ኢንድሮ ሞንታኔሊ ማን ነበር?

እንደነርሱ አቆጣጠር ከ1909 እስከ 2001 ድረስ የኖረው ይህ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ በፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ዘመን ነበር ወደ ፕሬስ ዓለም የተቀላቀለው።

ለፋሺስቶች ልሳን በነበረው 'ሰልቫጂዮ' ለሚባል ጋዜጣ ይሰራ ነበር።

ይህ በ1930ዎቹ ቤኔቶ ሙሶሎኒ ከሂትለር ጋር እጅና ጓንት ኾኖ አውሮፓን በሚያምስበት ዘመን መሆኑ ነው።

በ1935 እንደ አውሮፓዊያኑ ፋሺስቱ ሙሶሎኒ ወደ ኢትዮጵያ በርካታ ወራሪ ሠራዊት ሲልክ ይህ ጋዜጠኛ እኔም መዝመት እፈልጋለሁ ብሎ ተነሳ።

ለዚህ በዋናነት ወደ ሶማሊያና ከኤርትራ ለመጓዝ ከተሰባሰበው የጣሊየን ወራሪ ጦር፣ ለዚያ ለቅኝ ገዢዎች ሠራዊት ወዶና ፈቅዶ በወዶ ገብነት ተመዘገበ።

ሞንታኔሊ በኋላም በስፔን የእርስበርስ ጦርነት ጊዜም በፋሺስቶቹ ወገን ሆኖ ዜና ያቀርብ የነበረ ሰው ነበር። በ2ኛው የዓለም ጦርነትም ይህን ተግባሩን ቀጥሎበታል።

ከሥራው በጡረታ ከተገለለ በኋላ ይህ ሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እየተሰጠው መጣ።

በ2012 የዓለም የፕሬስ ኢንስቲትዩት ከዓለማችን የፕሬስ ጀግኖች አንዱ ሲል ሰየመው።

ዓለም አቀፍ ዕውቅናና መልካም ስሙ ታዲያ ሰውየው ለፋሺስት አስተዳደርና እና ለቅኝ ግዛት በነበረው መልካም አተያይ ሲጎድፍበት ቆይቷል።

ይህ ሰው ለረዥም ዘመን የፋሺስት ጦር በኢትዮጵያ አርበኞች ላይ የጋዝ መርዝ አልተጠቀመችም ሲል ክዶ የኖረ የዘረኝነት ጠበቃ ነበር።

"ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ የጋዝ መርዝ ተጠቅማለች የሚሉት በአምባ አራዳ ውጊያ ነው። እኔ እዚያው ነበርኩ። ያ ሲሆን አላየሁም። በሠራዊቱ ውስጥ የእኔ ሽርክ የነበረ ወዳጄ ሽንኩርት እንደሸተተው ነግሮኛል። የመርዝ ጋዝ ሽታ አልነበረም። ለዚያ ጦርነትስ የመርዝ ጋዝ አስፈላጊ ነበር ብላችሁ ነው? በዚያ አካባቢ ጠላትም አልነበረም እኮ…" ሲል ፋሺስት ጣሊያንን የተከላከለ ሰው ነው ይህ ሞንታኔሊ የሚባል ሰው።

በኋላ ላይ በ1996 አካባቢ አንጄሎ ዴል ቦካ የተባለ የታሪክ አዋቂ በማስረጃ ሲያፋጥጠው ግን በእርግጥም ጣሊያን ያን መጠቀሟን (መስታርድ ጋዝ) አምኗል።

ይህ ሰው ለረዥም ዓመታት ለዕለታዊው ኮሪየር ዴላ ሴራ ጋዜጣ ሲሰራ ቆይቶ በኋላ ላይ የቀኝ አክራሪዎች ልሳን የሆነውን ጂዮርናሌ የተባለ ጋዜጣን መሠረተ። ይህ በ1973 መሆኑ ነው።

ኋላ ላይ ቢሊየነሩ ሲልቪዮ በርልስኮኒ ይህን ጋዜጣ ሲገዛው ሞንታኔሊ ሥራ ለቀቀ።

በ1977 አንድ የቀኝ አክራሪ ሬድ ቢርጌድ አባል ሞንታኔሊን እግሩን በሽጉጥ ተኩሶት መትቶት ነበር፤ እዚያው ራሱ በመሰረተው ጋዜጣ በር ላይ ነው ክስተቱ የተፈጠረው። ሆኖም ሞንታኔሊ ቆሰለ እንጂ አልሞተም።

ሕይወቱ ያለፈችው በ2001 እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ነበር።