የሩሲያ ፍርድ ቤት አሜሪካዊው ላይ በስለላ ወንጀል የ16 ዓመት እስር ፈረደ

ፖል ዊለን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ፖል ዊለን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ይከራከራል

የሩሲያ ፍርድ ቤት የቀድሞ የአሜሪካ ጦር አባል ፖል ዊለን በስለላ ወንጀል የ16 ዓመታት እስክ ከከባድ የጉልበት ሥራ ጋር ፈረደበት።

ፖል ዊለን ከ18 ወራት በፊት ሞስኮ ውስጥ በአንድ የሆቴል ክፍል ውስጥ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት አገራዊ ሚስጢር የያዘ ዩኤስቢ (ፍላሽ ዲስክ) ይዞ ነበር ብሏል የሩሲያ ፖሊስ።

የሞስኮ ከተማ ፍርድ ቤት ፖል ዊለንን አገራዊ ሚስጢር በመቀበል በሚል ክስ ነው ጥፋተኛ ያለው።

ከአሜሪካዊነቱ በተጨማሪ፤ የዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አየርላንድ ዜጋ የሆነው ዊለን ጥፍተኛ አይደለሁም ሲል ይከራከራል። የቀረበበት ክስ እና የፍርድ ሂደት ሐሰተኛ መሆኑንም ተናግሯል።

በሞስኮ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ጆን ሱሊቫን የፍርድ ሂደቱ ሚዛናዊ እና ግልጸኝነት የጎደለው ነው ካሉ በኋላ፤ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአሜሪካ እና ሩሲያ ወዳጅነት ላይ ጉዳት ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፖል ዊለን ማነው?

የ50 ዓመቱ ፖል ዊለን የአራት አገራት ዜጋ ነው። የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አይሪሽ ሪፓብሊክ።

በሚሺጋን ግዛት ከልጅነቱ ጀምሮ በአሜሪካ ያደረገው ፖል፤ ከእንግሊዛውያን ቤተሰቦቹ የተወለደው ካናዳ ውስጥ ነበር።

በሚሺጋን ግዛት ለስድስት ዓመታት በፖሊስ አባልነት ያገለገለው ፖል፤ እአአ 1994 ላይ የአሜሪካ ጦር ኃይልን ተቀላቅሏል። ከዚያም እአአ 2004 እና 2006 ላይ ግዳጅ ለመወጣት ሁለት ጊዜ ወደ ኢራቅ ዘምቷል። የአሜሪካ ጦር አባል ሳለ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩሲያ ያቀናው። ከዚያም ለበርካታ ጊዜያት ሩሲያን ጎብኝቷል።

ከ18 ወራት በፊት በአንደ የሆቴል ክፍል ውስጥ በቁጥጥር ሥር ሲውል፤ በሠርግ ዝግጅት ላይ ለመታደም በዝግጅት ላይ ሳለሁ ነበር ይላል ፖል።

የሩሲያ ፍርድ ቤት ብይን ከተሰማ በኋላ የፖል ቤተሰቦች ባወጡት የጽሑፍ መግለጫ የሩሲያ ፍርድ ቤት ነው "በኢፍትሃዊነት ጥፍተኛ ሆኖ የተገኘው" ብለዋል።

ቤተሰቡ የፖል ዊላን ጠበቃ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይግባኝ ይጠይቃል ብለዋል። ፕሬዝደንቱም ጣልቃ ገብተው ፖልን ለምድሩ እንዲበቃ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።