ሰሜን ኮሪያ በድንበር የሚገኘውን ጊዝያዊ አገናኝ ቢሮ አጋየች

ቢሮው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር የተከፈተው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቢሮው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር የተከፈተው

ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ጋር የሚያቀራርባትንና ድንበር ላይ የሚገኘውን ጊዝያዊ ቢሮ በቦንብ አጋየች፡፡

ካዮሶንግ የድንበር ከተማ ይገኝ የነበረው ይህ ቢሮ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ አቁሞ ለአገልግሎት ዝግ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡

ሰሜን ኮሪያ ይህንን ቢሮ ስለማጋየቷ ደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናትም አረጋግጠዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ሰሞኑን በተደጋጋሚ "ተናድጃለሁ፤ ደቡብ ኮሪያ አናዳኛለች" ስትል አስታውቃ ነበር፡፡

ትናንት የኪም እህት ለሰሜን ኮሪያ የጦር ኃይል በተጠንቀቅ ላይ ሁኑ ብላ ትእዛዝ ሰጥታ ነበር፡፡

በሰሜን ኮሪያ ግዛት ድንበር ላይ ይገኝ የነበረው ቢሮ የተከፈተው ከ2 ዓመት በፊት ነበር፡፡ የጊዝያዊ ቢሮው አገልግሎትም ሁለቱን ወንድም ሕዝቦች ማቀራረብ ነበር፡፡

በዚህ የድንበር ከተማ ግንኙነት ለማደስ በሚል በ2003 ሁለቱ አገራት ግዙፍ የኢንዱስትሪ መንደር ከፍተው ነበር፡፡

በዚህ ኢንዱስትሪ መንደር 120 ፋብሪካዎች ተከፍተው 50ሺ ሰራተኞች ከሰሜን ኮሪያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሥራ አስኪያጆች ደግሞ ከደቡብ ኮሪያ ሆነው ምርት ያመርቱ ነበር፡፡

ኢንዱስትሪ መንደሩ በ2016 ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ሊያመሩ ነው በሚል ፍርሃት ተዘግቶ ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ እንዲከፈት ተደርጎ ነበር፡፡

በዚህ የድንበር ከተማ የሚገኘው የአገናኝ ቢሮ ታዲያ ሁለቱ አገራት በየጊዜው እየተገናኙ እንዲማከሩ የሚያግዝ ሆኖ ከ440 በላይ ሰራተኞች የነበሩት ቢሮ ነው፡፡ ሰራተኞቹ ግማሾቹ ደቡብ ኮሪያዊያን ሲሆኑ ቀሪዎቹ የሰሜን ተወላጅ ናቸው፡፡

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ታዲያ ሰሜን ኮሪያ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የታሰበው ንግግር ባለመሳካቱ ቢሮውን እዘጋዋለሁ ብላ ስታስፈራራ ነበር፡፡

ይህ አገናኝ ቢሮ በጊዝያዊነት የተዘጋው ባለፈው መስከረም የኮሮና ወረርሽኝ ተፈርቶ ነበር፡፡

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ድሮም ቋፍ ላይ የነበረ ሲሆን ፒዮንግያንግ ከአሜሪካ ጋር ንግግር ከጀመረች ወዲህ ግን የሁለቱን ወንድም-ሕዝቦች ጠላት መንግሥታት ለማቀራረብ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ፍሬ እያፈሩ ነበር፡፡

ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያ እያበሳጨችኝ ነው ማለት የጀመረችው አገሪቱን ከድተው በደቡብ ኮሪያ የተጠለሉ ዜጎቿ ፊኛ ወደ አገር ውስጥ መላክ ከጀመሩ ወዲህ ነው፡፡

በደቡብ ኮሪያ የወንድም ሕዝቦች ግንኙነት ሚኒስትር እንዳረጋገጡት ዛሬ በአገሬው አቆጣጠር ለ9 እሩብ ጉዳይ ላይ ፍንዳታ ተሰምቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የኪም እህት ኪም ዮ ጆንግ ወታደሮቿን ወደ ድንበር ለማስጠጋት ስትዝት ነበር፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኪም ጆንግ እህት ኪም ዮ ጆንግ

በኢውሃ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሌይፍ ኤሪክ የዚህ አገናኝ ቢሮ መውደም በሰሜንና ደቡብ ኮሪያ እየተሸሻለ የነበረው ግንኙነት ማክተሙን የሚያረዳ ነው ብለዋል፡፡

ፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ በዚህ መንገድ አካባቢውን ለማመስ በቀጣይነት ሌሎች እርምጃዎችንም ልትወስድ ትችላለች፤ ዋንኛ ፍላጎቷም በአሜሪካ የተጣለባትን ማዕቀብ እንዲላላላት መጠየቅ ነው፡፡

ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በ1953 ጦርነት ሲያበቁ የሰላም ስምምነት ስላላደረጉ አሁንም ደረስ ጦርነት ላይ እንዳሉ ነው የሚታሰቡት፡፡