ኮሮናቫይረስ፡ በቀብርና በሐዘን ሥነ ሥርዓት ላይ ከታደሙ ሰዎች 4ቱ ቫይረሱ ተገኘባቸው

ሰሜን ሸዋ

ባለፈው ሳምንት ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሆኖ በደረሰባቸው አደጋ በህክምና ላይ ሳሉ ህይወታቸው አልፎ ወደ ትውልድ መንደራቸው በተወሰዱ ግለሰብ ሐዘንና ቀብር ላይ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል በአራቱ ላይ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘ ተነገረ።

ባለፈው ሳምንት የምርመራ ውጤታቸው ሳይታወቅ አስከሬናቸው ከአዲስ አአበባ ወደ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በተወሰደው ግለሰብ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙና ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ገብተው ምርመራ መካሄዱን የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ጸዳለ ሰሙንጉሥ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"በሰዎቹ ላይ በተለያዩ ቀናት ምርመራ ተደርጎ በመጨረሻ ላይ ትላንት የወጣው ውጤት የ4 ናሙና ውጤት ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል" በማለት ግለሰቦቹ ወደ ህክምና ማዕክል እንዲገቡ ተደርጎ ከእነሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አራቱም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ምክትል ኃላፊዋ ንክኪ ያለቸውን ሰዎች የመለየቱ ተግባር እየተከናወነ ቢሆንም በቶሎ ምርመራ አድርጎ መለየት ደግሞ አስፈላጊው ቀጣይ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሽታው በማህበረሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚገልጹት ወ/ሮ ጸዳለ "ምርመራ ካለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ኮሮናቫይረስ ያልገባበት ቦታ አለ ብሎ ደፍሮ መናገር በጣም አስቸጋሪ ነው" ብለዋል።

በዚህም መሰረት በለይቶ ማቆያ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች በተጨማሪ ተጋላጭ ናቸው በሚባሉ የኅብረተሰቡ አባላት ላይ በማተኮር በመናኸሪያ አካባቢ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶችን በመለየት ከቅዳሜ ጀምሮ ደብረ ብርሃን ከተማ መደረጉን አመልክተዋል።

በዚህ መሰረትም 78 ሰዎችን ተመርምረው 22ቱ ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ምርመራው ከተደረገላቸው ሰዎች ውስጥ 36ቱ የመናኸሪያው ሾፌሮች እና ረዳቶች ሲሆኑ ከመካከላቸው 16ቱ ላይ ህመሙ እንዳለባቸው ታውቋል።

ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጠባቸው አሽከርካሪዎች አና ረዳቶች ውስጥ የተወሰኑት ብቻ ተገኝተው ወደ ለይቶ ማቆያ ማከሚያ አለመግባታቸውን የተናገሩት ወ/ሮ ጸዳለ "ከ16ቱ መካከል ዘጠኙን ክትትል እያገኙ ሲሆን ቀሪዎቹን እያፈላለገፍን ነው። ኅብረተሰቡም ግለሰቦቹ ህክምና እንዲከታታሉ እንዲጠቁም" ጠይቀዋል።

በዚህም ሳቢያ የዞኑ ጽህፈት ቤት በርካታ ሰዎችን ለመመርመር ህሙማንን ለመለየት ጥረት እየተደረገ በመደረግ ላይ መሆኑን አመልክተው፤ ባለፉት ቀናት ሰፊ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ውጤት እየጠበቁ እንዳሉ ወይዘሮ ጸዳለ አስታውቀዋል።

በቀጣይ ቀናትም በዞኑ ተጋላጭ ናቸው የሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመመርመር እየተሠራ እንደሆነና በዚህም ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች ሆቴሎች እና መሳሰሉት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ታውቋል።

ኮሮና
Banner