ቻይናዊውን ቢሊየነር ለማገት የሞከሩ ተያዙ

የቻይና 6ኛው ሂ ዣንግጂያን

የፎቶው ባለመብት, CCTV

የምስሉ መግለጫ,

የቻይና 6ኛው ቢሊየነር ሂ ዣንግጂያን

የቻይና መንግሥት ቻይናዊውን ዕውቅ ቢሊየነር ሚስተር ሂ ዣንግጂያን ለማገት አሲረዋል ያላቸውን አምስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገለጸ።

ሚስተር ሂ የቤት ቁሳቁሶች አምራች የሆነው የግዙፉ ማይዲያ ግሩፕ (Midea Group) ፈጣሪና ባለቤት ናቸው።

ማይዲያ ግሩፕ በዓለም ካሉ ታዋቂ የቤት ዕቃ አምራቾች ተርታ የሚሰለፍ እጅግ ግዙፍ ኩባንያ ነው።

ፖሊስ እኚህ ዕውቅ ቢሊየነር እየታገቱ መሆኑ የተነገረው በቢሊየነሩ ወንድ ልጃቸው በኩል ነው።

ባለፈው እሑድ አጋቾቹ በጓንግዶንግ አውራጃ፣ ፎሻን ከተማ የሚገኘውን የቢሊየነሩን ቪላ ቤት ሰብረው መግባታቸውን የተመለከተው የቢሊየነሩ ወንድ ልጅ በጓሮ በር ሹልክ ብሎ በመውጣት ከቪላ ቤታቸው አቅራቢያ የሚገኘውን ወንዝ እየዋኘ ከተሻገረ በኋላ ነገሩን ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግ ችሏል።

ሁሉም አጋቾች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን በማንም ላይ አደጋ እንዳልደረሰ ፖሊስ አስታውቋል።

የቢሊየነሩ የእገታ ድራማ በቻይና ማኅበራዊ ድር አምባ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። አንዳንዶች ክስተቱ ከሆሊውድ ድንቅ ፊልም አይተናነስም ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, CCTV

የምስሉ መግለጫ,

የቢሊየነሩ ቅምጥል ቪላ

አጋቾቹ እንዴት ተደረሰባቸው?

ፖሊስ ስለእገታው በስልክ መረጃ በደረሰው ቅጽበት በመንቀሳቀስ እገታውን አክሽፎታል።

ይህን የስልክ ጥሪ ፖሊስ ያገኘው ሊታገቱ ከነበሩት ቢሊየነር ከገዛ ልጃቸው ነበር። ልጃቸው የ55 ዓመት ሰው ሲሆን ሂ ጂያንፍንግ ይባላል።

ይህ የቢሊየነሩ ልጅ ግዙፉን የአባቱን ኩባንያ ከሚመሩት ዳይሬክተሮች አንዱ ነው። ይኸው ልጃቸው ነው ወንዝ በዋና አቋርጦ በመውጣት ለፖሊስ መረጃ አቀብሎ አባቱን ከእገታ ያስመለጠው።

አጋቾቹ ቦምብና ሌሎች መሣሪያዎችን ይዘው እንደነበር ፖሊስ ተናግሯል።

የቢሊየነሩ ሚስተር ሂ ጎረቤቶች 'ለቻይና ሞርኒንግ ሚዲያ' እንደተናገሩት ከእሑድ ማታ እስከ ሰኞ ማለዳ ማንም ሰው ከቤት እንዳይወጣ ተነግሯቸው ነበር፤ በዚህም ምክንያት ቤታቸውን ቆልፈው ተቀምጠዋል።

"በጣም ፈርቼ ነበር፤ እኔ ከሌላ ሰፈር የተሻለ ይህ ሰፈር ሰላማዊ ይሆናል ብዬ ነበር የማስበው፤ ይህ ይሆናል ብዬ አልጠበኩም" ብለዋል አንድ ጎረቤት።

የፎሻን ከተማ ፖሊስ በበኩሉ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አምስት አጋቾች በቁጥጥር ሥር ውለው ምረመራው እየተካሄደባቸው ነው።

ማይዲያ ኩባንያ እገታ ሙከራውን ተከትሎ በገጹ ላይ ፖሊስን፣ መገናኛ ብዙሃንን፣ እንዲሁም የአካባቢውን ሰዎች አመስግኗል።

ቢሊየነሩ ማን ናቸው?

ሚስተር ሂ ዣንግጂያን ከቻይና ቢሊየነሮች አንዱ ቢሆኑም ድምጻቸው እምብዛምም አይሰማም።

በ200 አገራት ቅርንጫፍ ያለው ማይዲያ የዓለም ቁጥር አንድ የቤት ቁሳቁስ አምራች ነው።

የሚስተር ሂ ሀብት ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል።

ፎርብስ እንደሚለው እኚህ ሰው በቻይና 6ኛው ቢሊየነር ናቸው። በዓለም ደግሞ 35ኛው ቢሊየነር ሆነዋል።

ሚስተር ሂ ገና የ26 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር በ1968 ከምንም ተነስተው ማይዲያ ኩባንያን የመሰረቱት።

ኩባንያው መጀመርያ የመኪና አካላትን በማምረት የጀመረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን የቤት ዕቃ አምራች አምራች ሆኖ የቢዝንስ ስኬትን ተቀዳጅቷል።

የአየር ማራገቢያ መሣሪያዎችን በማምረትም ዕውቅ ነው ማይዲያ።

የዓለም ቁጥር አንድ ሮቦት አምራች ኩባንያ የሆነውን የጀርመኑን ኩካ ኩባንያም የሚስተር ሂ ማይዲያ ገዝቶታል።

የኩባንያው ባለቤት እገታ ስለተሞከረባቸው የኩባንያው የዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች አንድ ቀን እረፍት ተሰትቷቸዋል።

ኩባንያው የሚለው ሠራተኞቹን እረፍት የሰጠነው አደጋ ካለ ያንን ለመፈተሸ ነው።