የቤት ውስጥ ጥቃት፡ "ባለቤቴ ቢላ ከኪሱ አውጥቶ አፍንጫዬን ቆረጠው"

ከቀዶ ጥገናው በኋላ ዛርካ ፊቷን ስትመለከት

የፎቶው ባለመብት, BBC

ከአስር ሳምንታት የማያባራ ስቃይ በኋላ ዛርካ የተስፋ ጭላንጭል ታያት።

"ደስ ብሎኛል። አፍንጫዬ ተመለሰ፣ ጥሩ ነው፣ በጣም ጥሩ ነው" ትላለች ዛርካ የታሸገውን አፍንጫዋን ለሚያክሟትና የቁስሉን ፋሻ እየቀየሩ ላሉት ዶክተሮች።

የተሰፋው አፍንጫዋ በፋሻ ቢሸንፍም የረጋ ደም ይታያል። ዛርካም ይህንኑ ፊቷን በእጅ መስታወቷ ትኩር ብላ ትመለከታለች።

በአፍጋኒስታን የቤት ውስጥ ጥቃት የተለመደ ነው፤ በከፍተኛ ሁኔታም ይፈፀማል። የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ የአገሪቱን መረጃ በመጥቀስ እንዳሰፈረው 87 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ቢያንስ አካላዊ፣ ወሲባዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

ሲከፋም በትዳር አጋሮቻቸው ወይም በወንድ ዘመዶቻቸው አሲድ ይደፋባቸዋል፤ በቢላም ይወጋሉ።

የዛርካም ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም ባላቤቷ ከኪሱ ቢላ አውጥቶ አፍንጫዋን ቆርጦታል።

የፎቶው ባለመብት, Dr Zalmai Khan Ahmadzai

"ባለቤቴ ሁሉንም ይጠራጠር ነበር" ትላለች ዛርካ። በመጠርጠር ብቻ አያቆምም፤ በሚወነጅላት ሰው እያመካኘም ይደበድባት ነበር።

ድበደባ የየቀን ኑሮዋ ነበር።

"ሁልጊዜም ሥነ ምግባር የጎደለኝ ሴት እንደሆንኩ ይነግረኝ ነበር። 'ፍፁም ሐሰት ነው' እለው ነበር" ትላለች።

የ28 ዓመቷ ዛርካ መደብደቧን ብትለምደውም ይህን ያህል ወደከፋ ደረጃ ይደርሳል ብላ አላሰበችም።

ማገገም

"ፈቴን በመስታወት ስመለከተው አፍንጫዬ እያገገመ ነው" በማለት ዛርካ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በማደንዘዣም ለሦስት ሰዓታት ያህል ቀዶ ህክምና አድርጋለች።

"ከቀዶ ጥገና በፊት ፊቴ ደስ የማይል ሁኔታ ነበር" ትላለች በሐዘን።

በአገሪቱ ካሉ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምናና ፊትን እንዲህ መልሶ ማስተካከል ከሚችሉ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ዛልማይ ካሃን አህማድዛይም ዛርካ እያሳየችው ባለችው ለውጥ መገረማቸውን ተናግረዋል።

"የቀዶ ህክምናው በጥሩ ሁኔታ ተካሂዷል። ምንም ያመረቀዘ ነገርም የለም፤ ሁሉ ጥሩ ነው" በማለት ዶክተር ዛልማይ ተናግረዋል።

ለዶክተሩ በባለቤቷ የፊቷ አካል ጎድሎ ለህክምና ስትመጣ ዛርካ የመጀመሪያዋ አይደለችም፤ በርካታ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው፣ በአባቶቻቸውና በወንድሞቻቸው የፊታቸው ክፍል ተቆርጦ ይመጣሉ።

የእስልምና እምነት ሕግጋት የፊት ክፍልን መቆራረጥን በፅኑ ቢቃወምም ይህ ጭካኔ የተሞላው ተግባር በቅድመ እስልምና አፍጋኒስታን ውስጥ ይፈፀም እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ።

ረዥሙ ጉዞ

ዛርካ ትውልዷ ከመዲናዋ ካቡል 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ካሪኮት ግዛት ነው። ቤተሰቦቿ ድሆች በመሆናቸው የትምህርት ዕድል አላገኘችም።

የፎቶው ባለመብት, Dr Zalmai Khan Ahmadzai

አካባቢው በታሊባን ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በመሆኑም ጥቃት በደረሰባት ወቅት በቀላሉ ቀየዋን ለቃ መውጣት አልቻለችም። የግዛቷ ፖለቲከኞችና ታጣቂዎች ተደራድረው ነው ወደ ካቡል ለህክምና መምጣት የቻለችው።

በዚያ ወቅትም ዶክተር ዛልማይ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ነበር፤ በሚያሳዝንም ሁኔታ ባለቤታቸውን በኮቪድ-19 አጡ። የ49 ዓመቱ ዶክተር ባለቤታቸውን ጃላላባድ ግዛት ቀብረው ዛርካን ለማከም ወደ ካቡል ተመለሱ።

"ለህክምና መጀመሪያ በመጣችበት ወቅት በመጥፎ ሁኔታ ላይ ነበረች። አፍንጫዋ ከመቆረጡ በተጨማሪ ቁስሉም አመርቅዞ ነበር" ይላሉ ዶክተር ዛልማይ።

ከሁለት ወራት በፊትም ማመርቀዙን እንዲቆምም የመከላከያ መድኃኒት ሰጧት። ከዚያም በወሩ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ተመለሰች።

ዛርካ ቢቢሲ የማገገሟን ሂደት እንዲቀርጽ እንዲሁም ስለደረሰባት ጥቃት በዝርዝርም ለመናገር ፈቃደኛ ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, Dr Zalmai Khan Ahmadzai

ባለቤቷም በእሷ እድሜ እንደሆነ የምትናገረው ዛርካ ይተዳደሩም የነበረው በእረኝነት ከሚያገኘው ገቢው ነበር። ለአስር ዓመት ያህል በትዳር ኖረዋል፤ የስድስት ዓመት ልጅም አላቸው።

"አጎቴ ነው ለእሱ በልጅነቴ የዳረኝ። በወቅቱ ህፃን ስለነበርኩም ስለ ህይወትም ሆነ ስለ ትዳር የማውቀው ነገር አልነበረም። እድሜዬም በትክክል ምን ያህል እንደሆነ አላውቅም" ትላለች።

ስለ ፈቃደኝነቷም ማንም እንዳልጠየቃት ታስታውሳለች።

ከዓመታት በኋላም አጎቷ የባለቤቷን እህት ለማግባት በመስማማት ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተገነዘበች።

"አጎቴ ለሚስቱ ጥሎሽ መክፈል ስላልቻለ እኔን እንደ ስጦታ እንደሰጠኝ ሰማሁ" ትላለች።

በአፍጋኒስታን አንዳንድ ቤተሰቦች ሴት ልጆቻቸውን ለመዳር ከሙሽራው ገንዘብ ይቀበላሉ ቢባልም ይህ ተግባር ህጋዊነት የለውም።

ከሠርጋቸውም በኋላ ዛርካ ባለቤቷ እህቶቹን እንደሚደበድብ ተረዳች፤ ነገር ግን ለምን እንደሆነ ብዙ አልገባትም።

"አደንዛዥ እፅ አይጠቀምም፤ የአዕምሮ ህመምም የለበትም" ትላለች።

"ለህይወቴ ፈራሁ"

በዓመታት የትዳር ህይወታቸው ውስጥ ባለቤቷ ሌላ ሚስት ለመጨመር አቅዶ ነበር። ለአንድ ወንድ በርካታ ሚስቶች ማግባት አዲስ ነገር አይደለም።

"እንደማይወደኝና ሌላ ሚስት ማግባት እንደሚፈልግ ነገረኝ" በማለት ዛርካ ታስታውሳለች።

ነገር ግን ባለቤቷ ለጥሎሽ መከፈል የሚገባውን ገንዘብ ማጠራቀም ባለመቻሉ ተስፋ መቁረጥና ንዴት ተጨምረውበት በየቀኑ የሚፈጽምባት ድብደባ እየከፋ ሄደ።

"ያለማቋረጥ ሲደበድበኝ ለህይወቴ እየፈራሁ መጣሁ" ትላለች።

አፍንጫዋ ከመቆረጡ በፊትም ድብደባው ሲከፋባት ግንቦት ወር ላይ ወደ አባቷ ዘንድ በመሄድ ነፃ እንዲያወጣት ተማፀነችው።

ነገር ግን ያለ እሱ ፈቃድ ወደ አባቷ ጋር በመሄዷ ባለቤቷ ፍለጋ መጣ።

የፎቶው ባለመብት, Dr Zalmai Khan Ahmadzai

"አንድ ምሽት ቤተሰቦቼ ጋር ካሳለፍኩ በኋላ በጠዋት ትልቅ ቢላ ይዞ መጣ። አባቴንም በቢላ እያስፈራራ እንዲሰጠኝ ጠየቀው። አባቴና የአጎቴ ልጅ ምስክሮች ካላመጣ አሳልፈው እንደማይሰጡት ነገሩት" ትላለች ዛርካ።

ባለቤቷም ምንም እንደማያደርጋት ቃል ገብቶ ምስክሮች ይዞ መጣ። ነገር ግን ስትመለስ የበለጠ ሁኔታዎች እየከፉ ሄዱ።

"ከቤተሰቦቼ ቤት በተመለስኩባት ዕለት ክፉኛ ደበደበኝ፤ ቢላም እያሳየኝ አስፈራራኝ" የምትለው ዛርካ "አፍንጫሽን እቆርጠዋለሁ" ብሎ ስላስፈራራትም ወደጎረቤት ሄዳ ተደበቀች።

ጎረቤቶቿ ጣልቃ ገብተው ቢያስጥሏትም ለጊዜው ነበር።

ከዚያም ተለማምጦ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት እንደሚወስዳት ቃል ገብቶ ወደ ቤቷ መለሳት።

ነገር ግን ጠመንጃ ይዞ የነበረው ባለቤቷ ዛርካን ከቤት ይዞ በመውጣት እየጎተተ ወደ አትክልት ቦታ ወሰዳት።

"እየጎተተኝም፤ 'ወደየት ነው የምትሸሺው?' ይለኝ ጀመር። አትክልት ቦታውም አነስ ያለ ነው። ከኪሱም ቢላ አውጥቶ አፍንጫዬን ቆረጠው" ትላለች።

የዛርካ ባላቤት አፍንጫዋን የሚቆርጠውም ያለእሱ ፈቃድ ቤተሰቦቿ ቤት በመሄዷ አዋርዳኛለች በሚል ስሜት ነው።

አፍንጫዋን ቆርጦም በደም ፊቷና ሰውነቷ በደም እንደተሸፈነ ጥሏት ሄደ።

"የተሰማኝን ህመም በቃላት መናገር አልችልም፤ በከፍተኛ ሁኔታም ደም እየፈሰሰኝ ነበር። መተንፈስም አልቻልኩም ነበር" ትላለች ህመሟን በማስታወስ።

ጩኸቷን በመስማት በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች ደረሱላት። የተቆረጠው የአፍንጫዋክፍል ተገኝቶ በአካባቢው ወደሚገኝ ጤና ማዕከልም ብትወሰድም ዶክተሩ አፍንጫዋን መልሶ ማያያዝ እንደማይችል ነገራት።

ዛክራ ልቧ ተሰበረ፤ ከደረሰባትም አካላዊ ጥቃትም ለማገገምም ሆነ አስቀያሚ ነኝ ከሚለው ስሜት መውጣት አልቻለችም።

አባቷና ወንድ ዘመዶቿ ተሰባስበውም የደረሰባትን ጥቃት ለመበቀልም ቢፈልጉትም ባለቤቷን ሊያገኙት አልቻሉም።

"'እንዴት እንዲህ አካልሽን ያጎድላል?' ብለው በጣም ተናደዱ። ቢያገኙትም እንደሚገሉት እየነገሩኝ ነበር" የምትለው ዛርካ አባቷና አጎቶቿም ምስክሮች የተባሉት ጋር ሄደው ቁጣቸውን በመግለጽ ጥይት ወደ ሰማይ ተኮሱ።

ቤሰቦቿ ባሏን አግኝተው ከመበቀላቸው በፊትም ፖሊስ ባለቤቷን በቁጥጥር ስር አዋለው።

ዛርካ በአካባቢው በሚገኘው ሆስፒታል ያደረገችው ህክምና በቂ አልነበረም። ፊቷን በተወሰነ መልኩ የሚያስተካክልላትንም እድል እየተመኘች ነበር።

"ምንም አይነት ቀዶ ህክምና እንዲደረግልኝና አፍንጫዬ እንዲመለስ ብቻ ነበር ምኞቴ" ትላለች።

ፊቷ በደም ተጨማልቆ የተነሳችው ፎቶም ብዙዎች መጋራታቸውን ተከትሎ የዶክተር ዛልማይን ትኩረት በማግኘቷ በነፃ ሊያክሟት እንደሚችሉ ቃል ገቡ። የምትኖርበት አካባቢ አስተዳደርም ወደ ዋና ከተማዋ ካቡል እንድትሄድ አደረገ።

ከዚያም የዶክተር ዛልማይ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ቀዶ ጥገናውን አከናወኑ።

ለቀዶ ህክምናው 2 ሺህ ዶላር ያህል ያስወጣት የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ ለመድኃኒት እስከ 500 ዶላር መክፈል ይኖርባት ነበር።

በነጻ ባገኘችው ህክምና አካላዊ ገፅታዋን ማስተካከል ቢቻልም ከደረሰባት የሥነ ልቦና ጉዳት በማገገም በራስ መተማመኗን መመለስ ጊዜ የሚጠይቅ ነገር ነው።

ልጄስ?

አሁን በዚህ ሰዓት በከፍተኛ ሁኔታ እያስጨነቃት ያለው ከባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር ያለው የልጇ ሁኔታ ነው።

"ልጄ ማሹቅን ለሦስት ወራት ያህል አይኑን አላየሁትም። በጣም ነው የምወደው። ልጄ ከእኔ ጋር እንዲሆን እፈልጋለሁ" ትላለች።

የባለቤቷን ጨካኝነትም አለማየቱ ባንድ በኩል አስደስቷታል።

ምንም እንኳን ልጇ ከባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር እንዳለ ብትሰማም ትክክለኛ አድራሻውን አታውቅም። የእራሷ የሆነ ገቢ ስለሌላትም የአገሪቱ ሕግ የማሳደጉን ኃላፊነት ለባለቤቷ ሰጥቶታል።

አሁን ከልጇ ጋር ተለያይቶ መኖሯ ቀን ተሌት እንቅልፍ የሚያሳጣት ጉዳይ ሆኗል።

"በጣም ነው የሚናፍቀኝ። ስበላ፣ ስጠጣ፣ ምንም ነገር ሳደርግ በአይኔ ላይ ይመላለስብኛል" ትላለች።

የዛርካ አባትና አጎቶቿ ልጁን ለማስመለስም ምንም እቅድ የላቸውም፤ ምክንያቱም ባለቤቷ ልጁን እጠይቃለሁ ብሎ በእሷ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ነገር ሲያስቡ ከፍተኛ ፍራቻ አላቸው።

ዛርካ ልጇ አብሯት እንዲኖር ብትፈልግም ነገር ግን ምንም ነገር ቢፈጠር ከባለቤቷ ጋር ድጋሚ በአንድ ቤት መኖር እንደማትፈልግ ታስረዳለች።

"ከእሱ ነፃ መሆን ነው የምፈልገው። አብሬው መኖርም ሆነ ስለሱ ማሰብ አልፈልግም። እሱን ስፈታውም ልጄን እንደማይሰጠኝ ሳስብ ጭንቅ፣ ጥብብ ይለኛል" ብላለች በሐዘን በሞላው ድምጽ።