ህንድ፡ የማህተመ ጋንዲ መነፅር 700 ሺህ ብር እንደሚያወጣ ተገምቷል

የማህተመ ጋንዲ መነፅር

የፎቶው ባለመብት, East Bristol Auctions Ltd

የምስሉ መግለጫ,

የማህተመ ጋንዲ መነፅር

የህንዳዊው ነፃነት ታጋይ ማህተመጋንዲ መነፅር በእንግሊዝ ለጨረታ ሊቀርብ መሆኑ ተሰምቷል።

በምስራቅ ብሪስቶል ግዛትም በሚገኝ የጨረታ ቦታም እንዲሸጥ በፖስታ ተልኳል።

የጨረታው አስተባባሪ አንድሪው ስቶው መነፅሩ 700 ሺህ ብር (15 ሺህ ፓውንድ) እንደሚያወጣ የገመተ ሲሆን ለኩባንያውም ታሪክ ነው ተብሏል።

የመነፅሩ ባለቤት ዋጋው ሲነገራቸው በድንጋጤ "ልባቸው ሸተት" ሊል ነበርም ተብሏል።

"መነፅሩን በፖስታ ሳጥናችን ውስጥ አንድ ሰው እንዳስገባውና ከዚያም ጋር ተያይዞ የማህተመ ጋንዲ መነፅር ሊሆን ይችላልም የሚል ማስታወሻም እንደሰፈረ አንድ ሰራተኛ ነገረኝ። እኔም በመጀመሪያ ብዙም ትርጉም አልሰጠሁትም ነበር እናም ዝም ብዬ ወደስራዬ ቀጠልኩ"ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነገር ግን አንድሪው ስቶው እንደሚሉት መነፅሩን ሲመረምሩት ህንዳዊው የነፃነት ታጋዩ መሆኑም ተረጋገጠ።

"የማህተመ ጋንዲ መነፅር መሆኑን ሳውቅ ከወንበሬ ልወድቅ ነበር። ባለቤቴንም ደውዬ ስነግረው እሱም በድንጋጤ ልቡ ሸተት ልትል ነበር" ብለዋል።

አስተባባሪው እንደሚሉት ባለቤቱ መነፅሩን ያገኙት ከትውልድ ወደ ትውልድ በመወራረሱ እንደሆነ ነግረዋቸዋል።

የቤተሰብ አባላቸውም በጎርጎሳውያኑ 1920 ማህተመ ጋንዲን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አግኝተዋቸው ከሳቸው እንደተቀበሉም ለአቶ አንድሪው አጫውተዋቸዋል።

"የነገሩንን ታሪክም ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠናል፤ ማህተመ ጋንዲ መነፅር ማድረግ ከጀመሩበት ጋር ጊዜው ተገጣጥሟል" የሚሉት አቶ አንድሪው የመጀመሪያ መነፅራቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።

ይኼንንም ግምት እንዲያስቀምጡ ያደረጋቸው የመነፅሩ ቁጥር ደከም ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው።

"የግል ንብረታቸውን ብዙ ጊዜም ስለሚሰጡ ይኸም መገኘቱ አይገርምም" ብለዋል።

መነፅሩን መግዛት የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን በተለይም ከህንድ ጥያቄዎች እየጎረፉ እንደሆነም ተናግረዋል።