አፍጋኒስታን፡ ምክር ቤቱ 400 የታሊባን እስረኞችን ለመፍታት ወሰነ

የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአፍጋኒስታን ከፍተኛ ምክር ቤት ከባድ ወንጀሎችን በመፈፀም ተከሰው የነበሩ 400 የታሊባን እስረኞችን ለመፍታት የቀረበውን ሃሳብ አፀደቀ።

ሎያ ጂርጋ ተብሎ የሚጠራው ምክር ቤት ውሳኔው የተላለፈው የሰላም ድርድር እንዲጀመር ለማስቻል እንደሆነ አስታውቋል።

አሜሪካ በአገሪቷ ያለው ወታደሮቿ ቁጥር በመጭው ሕዳር ወር ከ5 ሺህ በታች እንደሚሆን ካስታወቀች በኋላ ታሊባን በአፍጋኒስታንና በውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈፀምን ጨምሮ በሌሎች ወንጀሎች የተከሰሱ እስረኞቹ እንዲፈቱለት ሲጠይቅ ነበር።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይም አሜሪካና ታሊባን ለ19 ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለመፍታት የሰላም ስምምነት ለማካሄድ መስማማታቸው ይታወሳል።

የአሜሪካና የታሊባን አደራዳረዎችም ከአፍጋኒስታን መንግሥት ጋር ወደሚያደርጉት የሰላም ድርድር ከመግባታቸው በፊት 5 ሺህ የታሊባን እስረኞች እንዲፈቱ ተስማምተው ነበር።

በዚህም መሠረት በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን የቀሩት 400 እስረኞች ብቻ ነበሩ።

ከእነዚህ መካከል 150 የሚሆኑት የሞት ፍርድ የሚጠባባቁ መሆናቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ምክር ቤቱም እነዚህ እስረኞች እንዲፈቱ የወሰነው "የሚደረገውን የሰላም ስምምነት ሂደት ለመጀመርና እንቅፋቶቹን ለማስወገድ እንዲሁም ደም መፋሰሱን ለማስቆም" እንደሆነ ገልጿል።

ውሳኔውም በፕሬዚደንት አሽራፍ ጋኒም ይፈረማል ተብሏል።

በመንግሥትና በታሊባን መካከል የሚደረገው ድርድርም በሚቀጥለው ሳምንት ዶሃ እንደሚጀመር አንድ የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ የእስረኞቹ መፈታት ጉዳይ በነዋሪዎችና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ዘንድ አወዛጋቢ ሆኗል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ላለፉት 19 ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ከ32 ሺህ በላይ ንፁሃን ዜጎች መሞታቸውን ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት አመልክቷል።

ፕሬዚደንት አሽራፍ ጋኒም ከጎርጎሳውያኑ 2014 ጀምሮ ከ45 ሺህ በላይ የፀጥታ ኃይል አባላት መገደላቸውን በዚያው ዓመት ተናግረዋል።

ታሊባን ከ19 ዓመታት በፊት ከሥልጣን የተወገደው የመስከረም አንዱን ጥቃት ተከትሎ በአሜሪካ በተመራ ወረራ ሲሆን ቡድኑ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ አሁን ላይ ተጨማሪ ግዛቶችን ለመቆጣጠር ቀስ በቀስ የቀድሞ ጥንካሬውን አግኝቷል።

ቅዳሜ ዕለት የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ማርክ ቲ ኤስፐር በአፍጋኒስታን የሚኖራቸው ወታደሮች ቁጥር በመጭው ህዳር ወር ከ5 ሺህ ዝቅ እንደሚል ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም ህዳር ወር ላይ ከሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በፊት የወታደሮቹን ቁጥር ወደ 4 ሺህ ዝቅ ማድረግ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ባለፈው ሳምንት ነበር።