ቻዽ፡ 44 እስረኞች በአንድ ምሽት "በመርዝ ራሳቸውን አጥፍተዋል" መባሉ አወዛጋቢ ሆነ

የቻድ ሃይቅ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በቻድ እስር ቤት በአንድ ክፍል ውስጥ ከነበሩ እስረኞች መካከል አርባ አራቱ መሞታቸውን ተከትሎ የአሟሟታቸው መንስኤ አወዛጋቢ ሆኗል።

አቃቤ ህግ በበኮ ሃራም አባልነት ተጠርጣሪ ናቸው ያሏቸው እነዚህ እስረኞች በመርዝ ራሳቸውን ገድለዋል ቢሉም ምርመራው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው የሚያሳየው።

46 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሆነ ከፍተኛ ሙቀት፣ ውስጥ በአንድ ክፍል ተጨናንቀው በመታሰራቸው እንደሞቱ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት ኮሚሸን የምርመራ ውጤት አሳይቷል።

የኮሚሽኑ ሪፖርት የምርመራ ውጤት እንዳተተው ታሳሪዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ የተጨናነቀ፣ የሚያቃጥል በሚባል ሙቀት ክፍል ውስጥ ነው ታስረው የነበረው፤ ምግብና ውሃ ተከልክለዋል ብሏል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ግለሰቦቹ ታጣቂዎች ሳይሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው ብሏል።

የቻድ የፍትህ ሚኒስትር ድጂመት አራቢ በበኩላቸው የኮሚሽኑን ሪፖርት እንዲሁም የአቃቤ ህግጋቱን መረጃም በመውሰድ የእስረኞቹን አሟሟት የሚያጠናና አዲስ ምርመራ እንዲከፈት ማዘዛቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ታሳሪዎቹ ሚያዝያ አጋማሽ ላይ ከመዲናዋ ራቅ ብሎ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ሞተው ነው የተገኙት።

የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች 98 ክርስቲያን ወታደሮችን መግደላቸውን ተከትሎ ነው ጦሩ አካባቢውን ከታጣቂዎች ነፃ ለማድረግ በሚል የስምንት ቀናት ተልዕኮ ያደረገው።

በነዚህም ቀናትም አንድ ሺህ ያህል ታጣቂዎችን መግደላቸውን ያሳወቀ ሲሆን ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ደቢ ቻድን ከቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ነፃ አድርገናልም ብለዋል።

44ቱ እስረኞች አገሪቷ ባደረገችው የጦር ተልዕኮ 58 የቦኮ ሃራም ታጣቂ ተጠርጣሪዎች ተብለው ከተያዙት መካከል ናቸው፥

አርባዎቹ እስረኞች ወዲያው እንደተቀበሩና የአራቱ አስከሬን ደግሞ ለምርመራ ተልኮ መርዝ ተገኝቷል ተብሏል።

በህብረት ራሳቸውን እንዳጠፉና ከአያያዝ ጋር የተገናኘ ነው የሚለውንም እንደማይቀበሉ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል።

ነፃ የሆነው ኮሚሽን ግን አቃቤ ህግ ከሚለው በሙሉ ተቃራኒ ነው። ግለሰቦቹ አርሶ አደሮች እንደሆኑና የአካካቢውን ነዋሪዎችንም በዘፈቀደ እንዳሰሩ ገልጿል።

አገሪቷ የጦር ተልዕኮ አድርጌያለሁ ከምትለውም ጋር ጊዜው እንደማይገጥምም አስፍሯል።

ታሳሪዎቹ የተሰጣቸው ምግብም በቀን በቁጥር የሚቆጠር ተምር ሲሆን ለረሃብና ጥማትም ተጋልጠዋል ብሏል።

በአንድ ክፍል ውስጥ ከነበሩት እስረኞች መካከል ተራፊ የሆኑትን 14ቱ ለኮሚሽኑ እንደተናገሩት የሙቀት ሁኔታው በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በርካቶች ራሳቸውን ስተው መውደቃቸውንና ለእርዳታ ቢጣሩም ችላ እንደተባሉ ነው።

"እስረኞቹ ሙሉ ምሽቱን በፀሎት እንዲሁም ለእርዳታ ቢጣሩም ጠባቂዎቹ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋቸዋል" በማለትም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

የእስረኞቹ ሞትም በአካባቢው ቁጣን ቀስቅሷል።