ለማ መገርሳ፡ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሦስት አመራሮችን በጊዜያዊነት አገደ

Lema Megersa

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER

የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሦስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ አመራሮቹ ላይ ጊዜያዊ እገዳ ማስተላለፉን አሳወቀ።

የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ በኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን (ኦቢኤን) ላይ ቀርበው በፓርቲው ስለተላለፈው የእገዳ ውሳኔ ዕሁድ ምሽት ላይ እንደተናገሩት የመከላከያ ሚኒስትሩና የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ በጊዜያዊነት ታግደዋል።

በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን እንዲሁም ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የነበሩትና በኋላም የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ አማካሪ እንደሆኑ የተነገረላቸው ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ከታገዱት ውስጥ ናቸው።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው የኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ለሁለት ቀናት በክልሉ ውስጥ ስላለው ሁኔታና በፓርቲው ጉዳዮች ላይ ያደረገውን ውይይትና ግምገማ ሲያጠናቅቅ መሆኑ ተነግሯል።

አቶ ፈቃዱ እንዳሉት አቶ ለማ መገርሳ፣ ወ/ሮ ጠይባ ሐሰንና ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ከፓርቲው የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አልቻሉም በሚል ነው።

ጨምረውም እግዱ የተጣለባቸው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በነበራቸዉ ኃላፊነት ልክ ለመስራት ዝግጁ ሲሆኑ በማንኛውም ጊዜ መመለስ አንደሚችሉ ተናግረዋል።

ይህም በሦስቱ የቀድሞው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተላለፈው እገዳው ጊዜያዊ በመሆኑ ወደ ፓርቲው የመመለስ እድል እንዳላቸው ያመልክታል።

ከዚህ ባሻገርም ፓርቲው "ከ800 በላይ የወረዳ ባለስልጣናት፣ በከተማ እና በዞን ደግሞ 117 አመራሮች ላይ የማጽዳት ሥራ ለመስራት ተሞክሯል" በማለት በተለያዩ ደረጃዎች የተወሰዱ እርምጃዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

የአዲሱ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ቀጥለው ጎልተው ይታዩ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደርነት ተነስተው የመከላከያ ሚኒስትርነት ኃላፊነትን ከያዙ በኋላ ከዕይታ ርቀው ቆይተዋል።

አቶ ለማ ከቀድሞው ኢህአዴግ መክሰም በኋላ የገዢ ፓርቲነቱን ቦታ በተረከበው የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ ሂደት ላይ ጥያቄ እንዳላቸው በይፋ ወጥተው የተናገሩ ሲሆን፤ በካቢኔ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ባሻገር በፓርቲውም ሆነ በመንግሥት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ብዙም ሳይታዩ ቆይተዋል።

ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርነት ከተነሱ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ በከፍተኛ የአማካሪነት ቦታ ላይ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ከወራት በፊት ከወለዱ በኋላ በሥራ ቦታቸው ላይ እንዳልታዩ የቅርብ ሰዎች ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ከፓርቲው ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ ለኦቢኤን እንደተናገሩት ፓርቲው በወቅታዊ አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ መስጠቱን ገልጸዋል።

በስብሰባው የፓርቲው አመራር ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በኩል ክፍተት እንዳለና በዚህም ላይ ግምገማ ተደርጎ የማስተካከያ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።

ፓርቲው በተለይ የእገዳ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ከፍተኛ አመራሮቹ አቶ ለማ መገርሳ፣ ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን እና ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ከያዙት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መታገዳቸው ተገልጿል።

እገዳው በፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚጸድቅ ሲሆን እግዱ የተጣለባቸው አባላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ በሚሆኑ ጊዜ ግን ሊመለሱ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ጨምረውም ከፍተኛ አመራሩና አባላቱ "የፓርቲውን አቋም ይዞ በመታገል ላይ ክፍተት እንዳለ እንዲሁም ሌብነትም እንደ ተግዳሮት" ተጠቅሶ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም በጋራ ለመስራት ውሳኔ ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ባጋጠመው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነሐሴ 2 እና 3/ 2012 ዓ.ም በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ግምገማ ያካሄደ ሲሆን፤ በዚህም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ የክልሉና የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈውበታል።