ኒጀር፡ በኒጀር የእርዳታ ሠራተኞች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስድስት ፈረንሳያዊያን ተገደሉ

ይህ የተቃጠለ መኪና የተገኘው ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኒጀር ታጣቂዎች የእርዳታ ሠራተኞች ላይ ባደረሱት ጥቃት ስድስት ፈረንሳውያንንን እንዲሁም ሾፌርና አስጎብኚያቸውን መግደላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣት ገለፁ።

ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች በሞተር ሳይክል መጥተው ተኩስ መክፈታቸውን፣ የቲላቤሪ ክልል አስተዳዳሪ ቲጃኒ ኢብራሂም ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ፈረንሳያዉያኑ ጎብኚዎች የቀጭኔ መንጋ ለማየት በሚሰባሰቡባት ስፍራ ላይ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ተብሏል።

የፈረንሳይም መንግሥት የዜጎቹን ሞት አረጋግጧል።

የኒጀር መከላከያ ሚኒስትር ኢሶኡፎኡ ካታምቤ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ፈረንሳያውያኑ ለአንድ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት የሚሰሩ ነበር ብለዋል።

በዚህም አክትድ የተሰኘው የፈረንሳይ ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሠራተኞቹ በጥቃቱ መሞታቸውን ተናግሯል።

ፕሬዝዳነት ኢማኑኤል ማርኮን ከኒጀር አቻቸው ሞሐመዱ ኢሶኡፎኡ ጋር እሁድ ለት መነጋገራቸውን የወጣው መግለጫ ያስረዳል።

ቢቢሲ የተመለከተው ፎቶ የተገደሉት ግለሰቦች አስከሬን ከመኪናቸው ጎን መሬት ላይ ወድቆ በተጨማሪም የተቃጠለ መኪና በፎቶው ላይ ይታይ ነበር።

ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን ግልጽ ባይሆንም፤ በኒጀር ጂሃዳዊ ቡድኖች እየተስፋፉ በመሆናቸው እነሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠርጥሯል።

የፈረንሳይ መንግሥት ለዜጎቹ ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ መሰረት በአብዛኛው የኒጀር አካባቢዎች እንዳይሄዱ ያስጠነቅቃል።

ከዋና ከተማዋ ኒያሜ ውጪ እንዲሁም በድንበር አካባቢ ከፍተኛ የሽብር ጥቃት እንደሚያሰጋ የፈረንሳይ መንግሥት በዚሁ የጉዞ ማስጠንቀቂያው ላይ አስታውቋል።

ቦኮ ሃራምን ጨምሮ በአካባቢው በርካታ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ከአልቃኢዳ እና አይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች እንደሚገኙ ይነገራል።

ፈረንሳይ የአውሮፓ አገራት በምዕራብ አፍሪካ በታጣቂዎች ላይ የሚየያደርጉትን ዘመቻ ትመራለች።