ማኅበራዊ ሚዲያ፡ የ"ዊቻት" መዘጋት የቻይናና የአሜሪካ ጦርነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ይሆን?

ዊቻት፣ የቻይናና የአሜሪካ ባንዲራዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለዓለም አቀፉ የቻይና ማኅበረሰብ "ዊቻት" የተሰኘው መተግበሪያ ተራ የሞባይል ጌጥ አይደለም። ቤተሰብ ማለት ነው። ኑሮ ማለት ነው። ሕይወት ማለት ነው።

ለአሜሪካዊያን ፌስቡክ የሆነውን ያህል ለቻይናዊያን ዊቻት ነፍሳቸው ነው። ከወዳጅ ዘመድ መገናኛ ብቻም ሳይሆን ሽንኩርት ገዝተው ሒሳብ የሚከፍሉትም በዊቻት ነው።

አንዲት ቻይናዊት አገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቿንም ሆነ ጓደኞቿን የምትናፍቀው፣ ናፍቃም የምታገኛቸው፣ አግኝታም የምታወራቸው፣ አውርታም የምትስቀው በሌላ በምንም ሳይሆን በ"ዊቻት" በኩል ነው።

ለዚህም ነው ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ዊቻትን በተመለከተ ፍጹማዊ ውሳኔ (Executive order) ሲያስተላልፉ ቻይናዊያኑ ክፉኛ የደነገጡት።

ትራምፕ በዚህ ውሳኔያቸው ማንኛውም የአሜሪካ ኩባንያ ከዊቻት ጋር የሥራ ግንኙነት እንዳይመሰርት አዘዋል።

አንድ የሻንግሃይ ነዋሪ ለቢቢሲ ሲናገር "ዊቻት ለቻይና ቋንቋ ተናጋሪዎች የሕይወት ቁልፍ፣ የሕይወት ስንቅ ነው። የትም ዓለም ሁን ቻይናዊ ከሆንክ "ዊቻት" ቤተሰብህን የምታገኝበት ድልድይ ነው" ብሏል።

በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሉት ይህ የስልክ መተግበሪያ ሲጀመር እንደነ ፌስቡክ የማኅበራዊ መስተጋብር ድራምባ የነበረ ሲሆን ኋላ ላይ ግን ከቻይናዊያን ዕለታዊ ተግባር ጋር ቁርኝቱ እጅጉኑ እየጠበቀ መጥቷል።

አሁን በዊቻት ግብይት መፈጸም፣ ጌሞችን መጫወት የፍቅር ጓደኛ ማሰሻ፣ ትዳር መመስረቻም ጭምር ነው።

ይሁንና የደኅንነት ጉዳዮች የሚከታተሉና በዚሁ ረገድ አጥኚና አዋቂ የሆኑ ምሁራን እንደሚሉት ዊቻት የቻይና መንግሥት ዜጎቹን የሚሰልልበት ሁነኛው መሣሪያ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ እንደሚሉት ደግሞ ይህ መተግበሪ በአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ስጋት ደቅኗል። የተጠቃሚዎችን ዝርዝር መረጃ የሚቃርም ከመሆኑም በላይ የአሜሪካዊያንን ግላዊና የገንዘብ መረጃዎችን ይሰበስባል፣ ሰብስቦም ለቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በማቀበል ይታማል።

የዊቻት ባለቤት ቴንሴንት ኩባንያ ይህንን መተግበሪያ እስከ መስከረም አጋማሽ ለአሜሪካ ኩባንያ ካልሸጠ አሜሪካ ውስጥ መሥራት እንደማይችል እቅጩን ተነግሮታል።

ትራምፕ ያንን ይበሉ እንጂ በርካታ ቻይናዊያን በዊቻት ላይ የተቃጣውን እርምጃ በባህላቸው ላይ የመጣ አድርገው ነው የተመለከቱት። የቻይና ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የትራምፕን ውሳኔ "በብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሽፋን አሜሪካ ጠቅላይነቷን ለማጠናከር እየሞከረች ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

በዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የቻይና መንግሥት የተቆጣውን ያህል በአሜሪካና በተቀረው ዓለም በስደት ኑሯቸውን የሚመሩ ቻይናዊያንም ነገሩ አናዷቸዋል እንዲሁም ሐዘን ውስጥ ከቷቸዋል።

ከዚህ ተነስቶ የሁለቱ ኃያላን አገራት መቆራቆስ ወደለየለት ጦርነት መግባቱ አይቀርም ብለው የሰጉ ቻይናዊያንም አልጠፉም።

ዊቻት፡ የማይቀረው ጦርነት ማሟሟቂይ ይሆን?

ጄኒ 21 ዓመቷ ነው። በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት። ትራምፕ ዊቻትን ስለመዝጋታቸው ያወቀችው እራሱ ዊቻት መተግበሪያን በማሰስ ላይ ሳለች ነበር።

"መጀመሪያ እውነት አልመሰለኝም፤ ከዚያ ግን ነገሩ በጣም አስቆጣኝ" ብላለች ለቢቢሲ።

ጄኒ በቀን በትንሹ አራት ሰዓት ዊቻት ላይ ተጥዳ ታሳልፋለች። ቻይናም ሆነ አሜሪካ የሚገኙ ጓደኞቿን፣ ቤተሰቦቿን የምታገኛቸው በዊቻት አማካይነት ነው።

ሰዎችን ለማግኘት ብቻም ሳይሆን በቻይና ሚዲያዎች የሚታተሙ መረጃዎችን የምታገኘው በዊቻት በኩል ነበር።

የታይናንሜን የሰማዕታት ቀን ታስቦ ሲውል በዊቻት ሰሌዳዋ ላይ አንድ አረፍተ ነገር ጻፈች። ወዲያውኑ የዊቻት አካውንቷ ተዘጋ።

ለቢቢሲ እንደተናገረችው ዊቻት የእሷን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ እንዳይሰጥ ስጋት ቢኖራትም አሜሪካ ይህን መተግበሪያ ማገዷ ግን የምትቃወመው ጉዳይ ነው።

"አሜሪካ ያን ካደረገች ከቻይና መንግሥት በምን ተለየች?" ስትልም ትጠይቃለች፣ ጄኒ።

የጄኒ ዓይነት ቁጣ፣ ስጋትና ቅሬታ በርካታ ቻይናዊያን ላይ ተንጸባርቋል።

"አሜሪካ ሁሉን ባህል አካታች ትመስለኝ ነበር" ብላለች ማይሊ ሶንግ የተባለች በካሊፎርኒያ የምትኖር ቻይናዊት ስደተኛ ለቢቢሲ።

ሶንግ ከልጆቿ ጋር የምትገናኘው በዊቻት ነበር። ልጆቿን በዊቻት ነው የምታሳድገው ማለት ይቀላል።

"ምናልባት በአሜሪካ በርካታ ዜጎች በበሽታው እየሞቱ መሆናቸውና ምርጫው መቃረቡን ተከትሎ ትራምፕ ትኩረት ለማስቀየስ የወሰዱት እርምጃ" እንጂ ዊቻትን እስከመጨረሻው ሊዘጉት አይችሉም ብላ ተስፋ ተደርጋለች።

እሷን ከዊቻት ይልቅ እያስጨነቃት ያለው ግን ወደፊት ሁለቱ አገራት ወደለየለት ጦርነት እንዳይገቡ ነው።

ቻይና ምን እርምጃ ትወስድ ይሆን?

ሬቼል በአሜሪካ 10 ዓመት ቆይታ ነው ወደ ቻይና የተመለሰችው። የዊቻት ዜና የልጇ መርዶ ያህል ሆኖ ነው የተሰማት።

ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ይህን ነገረችው "ቻይና ውስጥ የምትኖር ከሆነ፣ ወደየትም ስትሄድ መዘንጋት የሌለብህ ሁለት ነገሮች አሉ። አንዱ ዊቻት ነው። ወተት ገዝተህ የምትከፍለው እንኳ በዊቻት ነው። ብዙ ቦታ ካሽ ገንዘብ የሚቀበል ሰው አታገኝም፣ ዊቻት ከሌለህ ወተትህን አታገኝም" ብላለች።

ዊቻት ከማኅበራዊ ድራምባነቱ ባሻገር የቻይና መንግሥት ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር ይጠቀምበት ነበር።

ቻይናዊያን ለጊዜው ቪፒኤን (virtual private networks) እየተጠቀሙ ዊቻትን ለመክፈት እየሞከሩ ነው። ቪፒኤን እግድ ወደተጣለባቸው ኔትወርኮች በአቋራጭ የሚያሳልፍ ቁልፍ ነው። አንድ አገር የተከፈተን ኔትዎርክ ሌላ አገር እንደተከፈተ አድርጎ መንግሥትን የሚያታልል መተግበሪያ ሊባል ይችላል።

አሁን ዊቻትን የታደገውም የቪፒኤን መኖር ነው።

ሬቼል በመጨረሻ ይህን ትላለች።

"አሜሪካንም ቻይናንም አይቻለሁ። ሁለቱም በጎም መጥፎም ጎን አላቸው። እኔ ግን ሁልጊዜም አማካይ ገለልተኛ ቦታ ለመያዝ እሞክር ነበር። ከዚህ በኋላ ገለልተኛ ሆኜ መቀጠል የምችል አይመስለኝም።"

ከሬቼል ቀጣይ እርምጃ ይልቅ ዓለምን እያስጨነቀ ያለው ቻይና አሜሪካንን በምን መንገድ ትበቀል ይሆን የሚለው ነው። መበቃቀሉስ የት ሲደርስ ነው የሚቆመው?