ሊባኖስ፡ በቤይሩቱ ፍንዳታ 2 ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ ሆነ

ተቃዋሚ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በቤይሩቱ ፍንዳታ ምክንያት የሞቱ ሰዎች አሃዝ ከሁለት መቶ በላይ ሲደርስ የሁለት ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸው እንዳለፈ በከተማዋ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ገለጸ።

ባለፈው ማክሰኞ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ ያጋጠመውን ከባድ ፍንዳታ ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በፍንዳታው ሰበብ ህይወታቸው ካለፈው ሰዎች ውስጥ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እንደሚገኙበት በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል የሆኑት አቶ ተመስገን ኡመር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ከፍንዳታው ጋር ተያይዞ የመቁሰል ጉዳት እንደደርሰባቸው የተረጋገጡ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ከሐኪም ቤት መውጣታቸውን የቆንስላው ኃላፊ ተናግረዋል።

አደጋው ከተከሰተ በኋላ የሊባኖስ መንግሥት ባወጣው የሟቾች ዝርዝር ውስጥ ስማቸውና ዜግነታቸው ያልተጠቀሱ ሰዎች በመኖራቸው የተለያዩ አገራት መንግሥታት ያልታወቁትን ሟቾች ለመለየት የማጣራት ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

ይህንን በተመለከተ ቆንስላ ጄነራሉ አቶ ተመስገን ኡመር ለቢቢሲ፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች አስከሬኖቹ ወደ ተቀመጡባቸው ስምንት ሆስፒታሎች በመሄድ ፍለጋ ማድረጋቸውንና ከሟቾቹ መካከል ኢትዮጵያዊ እንዳላገኙ አመልክተዋል።

ቆንስላው በቤይሩት ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያዊያን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንና ከፍንዳታው ጋር ተያይዞ የሚያስፈልጉ ነገሮችን እያከናወነ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

የቤይሩት ከተማ ዋና አስተዳዳሪ በማክሰኞው አውዳሚ ፍንዳታ ከ200 በላይ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ እንደሚታመን አመልክተዋል።

ባለስልጣኑ ማርዋን አቡድ ጨምረው እንደተናገሩት አብዛኞቹ ከውጭ አገራት የመጡ ሠራተኞች እንደሆኑ የሚታመኑ በርካታ ሰዎች ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።

የሊባኖስ ሠራዊት የፍንዳታው ዋነኛ ማዕከል በሆነው የወደብ አካባቢ ሲያካሂድ የነበረውን የነፍስ ማዳን ፍለጋ ሥራን ተልዕኮውን የመጀመሪያ ምዕራፍ አጠናቋል።

ባለፉት ቀናት የአገሪቱ መንግሥት ለደረሰው የፍንዳታ አደጋ በሰጠው ምላሽ ላይ ቁጣቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች ከፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል።

የፍንዳታ አደጋውን ተከትሎ አንድ ሚኒስትርና በርካታ የፓርላማ አባላት ከኃላፊነታቸው ቢለቁም በሕዝቡ ዘንድ የተቀሰቀሰው ቁጣ አልበረደም።

በዋና ከተማዋ ለደረሰው ከባድ ፍንዳታ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ በነበረ አሞኒየም ናይትሬት አማካይነት መሆኑን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።