ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ታይዋንን መጎብኘታቸው ቻይናን አስቆጣ

ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ታይዋንን መጎብኘታቸው ቻይናን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል ከታይዋን ፕሬዘዳንት ጋር መገናኘታቸው በቻይና እና አሜሪካ መካከል ያለውን ውጥረት አባብሶታል።

የጤና እና ሰብዓዊ አገልግሎት ጸሐፊው አሌክስ አዛር ባለፉት ዓሠርታት በደሴቷ ስብሰባ ካካሄዱ የአሜሪካ ፖለቲከኞች መካከል ከፍተኛው ናቸው።

ታይዋን ራስ ገዝ ብትሆንም ቻይና ተገንጥላ እንደወጣች ግዛቷ ትቆጥራታለች።

ቻይና፤ “የተዋሀደች ቻይና” በሚል የሰየመችውን መርህ አሜሪካ እንድታከብር ጠይቃለች።

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ፤ የአሜሪካው ባለስልጣን በታይዋን ጉብኝት እንደሚያካሂዱ ባለፈው ሳምንት ሲያስታውቁ፤ “ቻይና በአሜሪካና በታይዋን መካከል የሚካሄድ ማንኛውንም ይፋዊ ግንኙነት ትቃወማለች። የቻይናና የአሜሪካ ግንኙነት እንዳይሻክር፤ አሜሪካ የታይዋንን ራስ ገዝነት በተመከለከተ የተሳሳተ መልዕክት እንዳታስተላለፍ እናሳስባለን” ብለው ነበር።

የአሜሪካው የምክር ቤት አባል፤ ታይዋን የደረሱት ከታይዋኑ ፕሬዘዳንት ዚ ኢንግ-ዊን ጋር ከተወያዩበት አንድ ቀን ቀድመው ነበር። ጉብኝቱን ያካሄዱት በሦስት ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።

“የመጀመሪያው ምክንያት ታይዋን ነፃ እና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ስለመሆኗ እውቅና ለመስጠት ነው” ብለዋል።

አያይዘውም፤ “ሁለተኛው ምክንያት ታይዋን የአሜሪካ የረዥም ጊዜ ወዳጅና አጋር መሆኗን ለማሳየት ነው። ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ታይዋን ለዓለም አቀፍ ጤና ጥበቃ ላበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና ሊሰጣት እንደሚገባ ለመጠቆም ነው” ብለዋል።

አሜሪካ ከታይዋን ጋር ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ባይኖራትም፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 1979 ላይ የተፈረመ ስምምነት፤ አሜሪካ ለታይዋን መሣሪያ እንድትሸጥ እንዲሁም “ቅርብ ትስስር እንዲፈጥሩ” ይፈቅዳል።

በታይዋን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ480 በታች ሲሆን፤ ሰባት ሰዎች ሞተዋል።

ታይዋን፤ ከቻይናዋ ውሃን ግዛት የሚነሱ በረራዎችን ጥር 23 ነበር ያገደችው። ወደ ታይዋን የሚገቡ ሰዎች ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ማድረግና በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውንም መለየትም ችላለች።

በቻይና እና በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያልተሰጣት ታይዋን የዓለም ጤና ድርጅት አባል አይደለችም።

ታህሳስ ላይ የታይዋን መንግሥት ከዓለም ጤና ድርጅት ስለ ኮቪድ-19 ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ እንዳልተሰጠው ተገልጿል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚያዝያ ላይ የዓለም ጤና ድርጅትን የሚተች ትዊት ሲጽፉ ይህን ጉዳይ ጠቅሰው ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፤ ከታይዋን በተላከው ኢሜል ስለ በሽታው ከሰው ወደ ሰው ተላላፊነት አልተጠቀሰም ብሏል።