ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ፡ ጉዳያቸውን በሚመለከቱ የዳኛ ገለልተኛነት ላይ ጥያቄ አነሱ

አቶ በቀለ፣ ጃዋርና ሐምዛ

ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ጃዋር መሐመድና ሌሎች 14 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸውን በሚመለከቱት ዳኛው ገለልተኛነት ላይ ጥያቄ እንዳነሱ ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ገለጹ።

ጠበቃው እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዎቹ “ችሎቱን እየመሩ ያሉት ዳኛ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ስለመሆናቸው እንጠራጠራለን” ሲሉ ባለ ሰባት ገጽ ማመልከቻ አስገብተዋል።

በማመልከቻው ላይ አቶ ጃዋር “ዳኛው የፌዝ ሳቅ ስቀው ነው ያስተናገዱኝ” ማለታቸውን ከአሥሩ ተከላካይ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ አክለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ዳኛው እንዲነሱ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ችሎቱን እየመሩ የሚገኙት ዳኛ ግን ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርገውታል። የተጠርጣሪዎቹ ጥያቄ በሌሎች ዳኞች ታይቶ ብይን እስከሚሰጥ ድረስ መዝገቡ ተዘግቶ ተጠርጣሪዎቹ ባሉበት እንዲቆዩ መወሰኑንም ተናግረዋል።

ጠበቃው ለቢቢሲ እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዎቹ ባስገቡት ማመልከቻ ላይ “ዳኛው ለከሳሽ ወግነው ጉዳዩን እየመሩ ስለሆነ ይነሱልን” ሲሉ ጠይቀዋል።

በሕጉ መሠረት፤ እንዲህ አይነት ጥያቄ ሲቀርብ፤ ዳኛው ጥያቄውን ተቀብለው ከችሎት ካልተነሱ ጉዳዩ በሌሎች ዳኞች የሚታይ ይሆናል።

አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 14ቱ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት የቀረቡት አቃቤ ሕግ በቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለዛሬ ቀጥሮ በመስጠቱ ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በቀዳሚ ምርመራ ከሚያቀርባቸው 15 ምስክሮች መካከል አምስቱ ማንነታቸው ሳይገለጽ [ከመጋረጃ በስተጀርባ] ቃላቸውን እንደሚሰጡ ባለፈው ሳምንት መገለጹ ይታወሳል።

አቶ ቱሊ እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዎቹ ችሎቱን የሚመሩት ዳኛ ገለልተኛነት ላይ ጥያቄ ካነሱበት ምክንያት አንዱ “የመሰማት መብታችን ተገድቧል” ብለው ነው።

“ተጠርጣሪዎቹ፤ ዳኛው በጠበቆቻችን የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን በአግባቡ እየሰሙ አይደለም ብለዋል። ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ይመስክሩ የተባሉ ሰዎች ማንነታቸው ሳይገለጽ የሚመሰክሩበት ሁኔታ አለ ወይስ የለም? በሚለው ላይ መከራከሪያ ለማቅረብ ብንጠይቅም ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም” ብለዋል።

በሕጉ መሠረት የአገር ደኅንነትን የሚጎዳ ጉዳይ ሲሆን ወይም ምስክሮች ለደኅንነታቸው ሲሰጉ ማንነታቸው ሳይገለጽ ቃላቸውን ለመስጠት ዐቃቤ ሕግን ይጠይቃሉ።

ጠበቃው እንደሚሉት፤ ዐቃቤ ሕግ ከመጋረጃ በስተጀርባ ይመስክሩ ያላቸው አምስት ግለሰቦች፤ ማንነታቸው ሳይገለጽ ቃላቸውን መስጠት እንደሚፈልጉ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ውል የገቡበትን ሰነድ ለፍርድ ቤት አላቀረበም።

“ዐቃቤ ሕግ እነዚህ [ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጽ ቃል ለመስጠት የጠየቁበት ሰነድ] ባልተሟሉበት ሁኔታ ምስክሮቹ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ይመስክሩ ማለቱን አልተቀበልንም” ይላሉ አቶ ቱሊ።

ጠበቃው እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዎቹ ባስገቡት ማመልከቻ ላይ የችሎት ሂደቱን ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ የግል የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች እንዲዘግቡ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ እንዳደረገው ጽፈዋል።