ኮሮናቫይረስ፡ በአውስትራሊያ የተከሰተው አዲሱ ዙር ወረርሽኝ ከለይቶ ማቆያ ሆቴሎች ጋር የተገናኘ ነው ተባለ

ሜልቦርን ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአውስትራሊያዋ ከተማ ቪክቶሪያ የተከሰተው አዲሱ ዙር ወረርሽኝ ከለይቶ ማቆያ ሆቴሎች ጋር የተያያዘ መሆኑ ተገልጿል።

ከሌላ አገራት የተመለሱ መንገደኞች ራሳቸውን ለይተው ባቆዩባቸው ሆቴሎች ወረርሽኙ መነሳቱም በምርመራ ተጣርቷል።

በዚህ ምርመራ እንደተገኘው የሆቴሉ አጠቃላይ ሰራተኞችም ያልተገባ ስልጠና ወስደዋል ተብሏል።

የአውስትራሊያ ሚዲያ እንደዘገበው የሆቴሉ ጠባቂዎች ጭምብልም ሆነ ሌሎች የመከላከያ ቁሳቁሶችን ማድረግ አስፈላጊ አይደለም፤ አካላዊ ርቀታችሁን እስከጠበቃችሁ ድረስ የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ ቪክቶሪያ ላይ አዲስ ዙር ወረርሽኝ ተከስቷል፤ ከተማው እንቅስቃሴዋ እንዲታገድ ትዕዛዝ ተላልፏል።

በሌላኛዋ ከተማ ሜልቦርን እንዲሁም ጥብቅ የተባለ የእንቅስቃሴ ገደብ ለስምንት ሳምንታት ተጥሎባታል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በቪክቶሪያ 282 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 25ቱ ሞዋል። ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮም ከፍተኛ እንደሆነም ተገልጿል።

መጋቢት መጨረሻ ላይ የአውስትራሊያ ፌደራል መንግሥት በሌላ አገራት የሚኖሩ ዜጎቹ ሲመለሱ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት አለባቸው የሚል ውሳኔን አስተላልፏል። ይህንንም ተግባራዊነት የሚያስፈፅሙት የተለያዩ ከተማ አስተዳዳሪዎች ናቸው።

በሜልቦርን የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ቤን ሃውደን እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የተከሰተው አዲሱ ዙር ወረርሽኝ ውስጥ 99 በመቶው ከውጭ አገራት ከመጡ መንገደኞች ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

ስለ መንገደኞቹ ማንነትም ሆነ የትኞቹ ሆቴሎች እንደሆኑ ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

ምርመራው ሆቴሎች ለይቶ ማቆያዎቻቸውን እንዴት እያስተዳደሩ እንደነበርም በምርመራው በጥልቀት እየታየ ነው ተብሏል፤ ይህም ለወደፊቱ ለይቶ ማቆያዎች በማሻሻያነት ግብአት እንዲሆን ነው።

ለይቶ ማቆያዎቹ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መግታት ሳይሆን የበለጠ ማስፋፊያ ሆነዋልም ተብሏል።