ሥራ ፈጠራ፡ ኮካ እና ፔፕሲን ያሸነፉት ሁለቱ ተማሪዎች

Kola ፍሪትዝ ኮላ

የፎቶው ባለመብት, Fritz-Kola

የምስሉ መግለጫ,

ፍሪትዝ ኮላ ለገበያ የቀረበው እኤአ በ2003 ነው

ማይክሮ ሜይገርት እና ሎሬንዝ ሃምፕል የኮላ ኩባንያ ለመመስረት ሲያስቡ ተማሪዎች ነበሩ። ተማሪ መሆን ብቻ ሳይሆን የለስላሳ መጠጥ እንዴት ማምረት እንደሚችሉ ፈጽሞ እውቀቱ አልነበራቸውም።

የወጣትነት ልበ ሙሉነትና ተስፋ በደም ስራቸው ይራወጣል፤ የይቻላል መንፈስ ከፊታቸውን ያለ ተግዳሮት ሁሉ አስረስቷቸዋል። ለምን ትንሽ ጎግል ላይ የተወሰነ ነገር አናነብም ሲሉ ወሰኑ።

" ኮላን ለመስራት የሚያገለግሉ ንጥረ ነገሮችን ጎግል ላይ አሰስን" ይላል ማርኮ፤ በወቅቱ የ28 ዓመት ወጣት ነበር።

በይነ መረቡ ግን የኮላን ምስጢር በመስጠት ስራቸውን ሊያቀልለው አልፈለገም፤ ስለዚህ እነዚህ ሁለት የልጅነት ጓደኛሞች ሌላ አማራጭ መፈለግ ነበረባቸው።

ሁለቱ ጓደኛሞች በሰሜናዊ ጀርመን ሃምቡርግ ነው ያደጉት፤ ስልካቸውን አንስተው ወደ ተለያዩ የቢራ ጠማቂዎች ዘንድ ደወሉ፤ ተስፋቸው ኮላ መስራት የሚያስችል ንጥረ ነገር በመቀመም እንዲረዷቸው እንዲሁም መጠጡን እንዲያሽጉላቸው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Valeska Achenbach

ነገር ግን በወቅቱ ሁሉም ቢራ ጠማቂዎች ጀርመን አለኝ የምትለውን ፒልስነር የተሰኘ መጠጥና ሌሎች ቢራዎችን በመጥመቅ ተጠምደው ነበር።

ማይክሮ እንደሚለው ከሆነ "በመቶዎች የሚቆጠሩ" ጠማቂዎች ጋር ደውለዋል። ደግሞም ጥሪያቸውን የመለሱት ጠማቂዎችም ቢሆኑ ወጣቶቹ ለምን ለስላሳ መጠጥ ማምረት እንደፈለጉ በጥርጣሬ ተሞልተው ይጠይቋቸው ነበር።

አንድ ሰው ግን እሺ አላቸው።

" በስተመጨረሻ በምዕራብ ጀርመን አንድ አነስተኛ የቢራ መጥመቂያ ባለቤት ከእኛ ጋር ለመስራት ተስማማ" የሚለው ማይክሮ " የጠመቃ ባለሙያው ' ኑና ጎብኙኝ እናም የሆነ ነገር እንሰራለን' " እንዳላቸው ያስታውሳል።

በዚያ ዓመት መጨረሻ ላይ ማይክሮ እና ሎሬንዝ 170 ሳጥን የፍሪትዝ ኮላ አምርተው ለመሸጥ አዘጋጁ። 170 ሳጥን ወደ 4,080 ጠርሙስ ገደማ እንደሚደርስ ይናገራሉ።

ይህንን ምርት ይዞ ወደ ትልልቅ የገበያ አዳራሾችና ሌሎች ቸርቻሪዎች ጋር ከመሄድ በቀጥታ መጠጥ ቤቶች እየሄዱ ማከፋፈልን መረጡ።

ሁለቱም ለስላሳቸውን በመኪናዎቻቸው ላይ ጭነው ሃምቡርግ ውስጥ በሚገኙ መጠጥ ቤቶች እየዞሩ በቀጥታ ለመሸጥ ሞክረዋል።

አሁን የለስላሳ መጠጡ ስም በመላው ጀርመን ይታወቃል። ባለፈው ዓመት ብቻ ከኮካ ኮላ ቀጥሎ የተሸጠ የለስላሳ መጠጥ ምርት ነው። ባለፈው ዓመት 71 ሚሊዮን ጠርሙስ ለስላሳ መጠጥ መሸጣቸውን ገለልተኛ የሆነ የገበያ ጥናት ቡድን አረጋግጧል። በወቅቱ ኮካ ኮላ 74 ሚሊዮን ሲሸጥ ፔፕሲ ደግሞ 337,000 ሸጧል።

በርግጥ ኮካ እና ፔፕሲ በፕላስቲክና ቆርቆሮ የታሸጉ መጠጦቻቸው በብዛት ተሸጠዋል። ቢሆንም 17 ዓመት እድሜ ላለው ለጋ የንግድ ሃሳብ ትልቅ ስኬት ነው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Florent Jalon

የምስሉ መግለጫ,

የለስላሳ መጠጡ ምርት ለአምስት ፋብሪካዎች ተሰጥቷል

በ2003 ማይክሮ እና ሎሬንዝ የራሳቸውን ምስል ለንግድ አርማ ምልክትነት ለመጠቀም ወሰኑ። ማይክሮ ይህንን ለምን እንደመረጡ ሲናገር ያለው ርካሽ አማራጭ በወቅቱ እርሱ ነበር ይላል።

"ፊታችንን እንዲህ አድርጎ ለማሳመር የከፈልነው 100 ዩሮ ብቻ ነው" ይላል ማይክሮ። " ጎረቤታችንን ፎቷችንን በፎቶሾፕ እንዲሰራውና ብራንዳችንን ለማስመዝገብ የከፈልነው 70 ዩሮ ነው እናም የራሳችንን የፍሪትዝ ኮላ ፎንት ፈጠርን" ብሏል የ44 ዓመቱ ማይክሮ።

ለጓደኛሞቹ በወቅቱ የባለቀለም ህትመት ውድ ስለነበር በጥቁርና ነጭ ማስጻፍንም መርጠዋል።

የምርታቸውንም ስም ለማውጣት የመረጡት ተጠቃሚዎች እንዲመርጡ ማድረግን ነው። 40 ያህል ስሞችን በወረቀት ላይ ካሰፈሩ በኋላ ከአንድ የመገበያያ ስፍራ ውጪ የተሰባሰቡ ሰዎች እንዲመርጡ አደረጉ። በጀርመኖች ዘንድ የተለመደው ስም፣ ፍሪትዝ ተመረጠ።

መጠጡም ላይ ቢሆን ጣዕሙ ከኮካ ኮላ ወይንም ከፔፕሲ እንዲለይ ፈልገዋል። ስለዚህ አነስተኛ የስኳር መጠን እንዲሁም የሎሚ ጭማቂ ጨምረውበታል። በተጨማሪ ደግሞ ከሌሎቹ ላቅ ያለ ካፌይን መጠቀማቸውን ማይክሮ ይናገራል።

"የኛን ኮላ ስትጠጡ በጣም ጣፋጭ አይደለም ነገር ግን ጠንከር ያለ ካፌይን አለው" የሚለው ማይክሮ፣ ስለዚህ ገበያውን ከሚመሩት ለስላሳ መጠጦች በበለጠ ሁኔታ በሶስት እጥፍ ካፌይን መጨመራቸውን ገልጿል።

ማይክሮ መጀመሪያ አካባቢ የእነርሱን ምርት ተቀብሎ ለማከፋፈልም ሆነ ለመሸጥ ፍላጎት የነበረው ድርጅት አለመግኘታቸውን ያስታውሳል። " በርካታ ሰዎች ከለመዱት ኮላ ይልቅ የኛን ለመጠጣትም ሆነ ለመመኮር አይፈልጉም ነበር።"

የመጠጥ ቤት ባለቤቶችንና ኃላፊዎችን ለማሳመን፣ አልሸጥ ያላቸውን መጠጥ ለመመለስ እና የከፈሉትን ዋጋ ለመመለስ ቃል በመግባት ማከፋፈል ጀመሩ።

እነ ማይክሮ ቀን ተሌት ደክመው መስራታቸው ፍሬ አፈራ እና መጠጣቸው ተወደደ። ወጣቶቹ ማይክሮና ሎሬንዝ ይዘ ውየመጡትን የለስላሳ መጠጥ ያስተዋሉ ደንበኞች "እስቲ እንሞክረው" በማለት እድል ሰጥዋቸው።

ማይክሮና ሎሬንዝ የራሳቸውን ቢሮ ለመክፈትም ሆነ የመጀመሪያውን ሰራተኛ ለመቅጠር ሶስት ዓመት ፈጅቶባቸዋል። እስከዚያ ድረስ ቢሮ እንኳ አልነበራቸውም።

ነገር ግን ምርታቸው ተጠቃሚዎቹ እየወደዱት በመጡ ቁጥር ዝናው እየናኘ መጣ። መደበኛ ማስታወቂያ ከማስነገር ይልቅ ዝናውን ተጠቃሚዎች እየተቀባበሉት፣ የሰሙት ላልሰሙት እያዳረሱ ሄዱ።

ዛሬ ለስላሳ መጠጣቸው በመላው አውሮጳ መጠጥ ቤቶችና ሱቆች ውስጥ ይሸጣል። ከጀርመን በኋላ ዋነኛ ገበያቸው ኔዘርላንድስ፣ ፖላንድ፣ ቤልጂየም እና ኦስትሪያ ነው።

በአሁን ሰዓት ፍሪትዝ ኮላ በአምስት ፋብሪካዎች ውስጥ እየታሸገ የሚከፋፈል ሲሆን ከስኳር ነፃ፣ በተለያየ የፍራፍሬ ጣዕም ማምረት ጀምሯል።

ምንም እንኳ ድርጅቱ የገቢና ወጪውን አስልቶ ይፋ ባያደርግም ፎርብስ ግን በ2018፣ በ2015 የድርጅቱ ሽያጭ 7.4 ሚሊዮን ዩሮ እንደነበር ገልጿል።

ከ2016 ጀምሮ ማይክሮ ሃምቡርገግ የሚገኘውን ንግዱን እየመራ የሚገኝ ሲሆን፣ ሎሬንዝ ግን በዚያ ዓመት ከጓደኛው ጋር በመለያየት ሌላ ስራ ላይ ለመሰማራት ወስኗል።

ማይክሮ በአሁኑ ሰዓት የድርጅቱን ሁለት ሶስተኛ በባለቤትነት ሲይዝ ሌሎች ባለሃብቶች ደግሞ አንድ ሶስተኛ ድርሻውን ይዘዋል።

ከ17 ዓመት በፊት ማንም አላመነንም ነበር የሚለው ማይክሮ፣ 'በዓለም ላይ ትልቅ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር ለመፎካከር የምትፈልጉት ምንኛ ጅል ብትሆኑ ነው' መባላቸውን ያስታውሳል።

ነገር ግን ለሁለቱ ጓደኛሞች ይህ የፈጠራ ሃሳብ ደስታን የሚፈጥር እና የበለጠ ታግለው ማሸነፍ የሚፈልጉት ተግዳሮት ሆኖ ነበር የተሰማቸው።

"ዛሬ 280 ሰዎች ቀጥሬ አሰራለሁ። በኩባንያ ውስጥ በቂ የሆነ ውጣ ውረድ አለኝ፤ ስለዚህ ሌላ ነገር መስራት አልፈልግም። የምሰራውን እወደዋለሁ" ይላል።