ልደቱ አያሌው፡ ኢዴፓ አቶ ልደቱን በሚመለከት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ደብዳቤ ሊጽፍ ነው

አቶ ልደቱ አያሌው

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ዛሬ ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

አቶ ልደቱ ዛሬ ችሎት የቀረቡት ባለፈው ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ በተሰጠው ሰባት ቀናት መሰረት ነው።

ጉዳያቸውን በቅርበት የሚከታተሉት የፓርቲው ፕሬዚደንት አቶ አዳነ ታደሰ ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንዳላቀረበ ገልፀው፤ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ አቶ ልደቱ ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ የሕክምና ማስረጃ እንዲያቀርቡ በጠየቀው መሠረት የህክምና ማስረጃ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።

የሕክምና ማስረጃዎቹ ህመማቸው ለሕይወታቸው አስጊ መሆኑንና ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ መሆናቸውን እንዲሁም የሕክምና ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልፁ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ የሕክምና ቀጠሮ እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረባቸውንም አቶ አዳነ ገልፀውልናል። ነገር ግን ይህንን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ለማየት ተጨማሪ የሰባት ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ ልደቱን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የሃጫሉን መገደል ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርጥረው መሆኑ መገለፁ ይታወሳል።

አቶ አዳነ ዳኞቹ በተለያየ ጊዜ በመለዋወጣቸው እና ጉዳዩ አዲስ እየሆነ በመምጣቱ እንደገና የሰባት ቀን ቀጠሮ ሊሰጣቸው ችሏል ብለዋል።

ፖሊስ 'ቤታቸውን ስበረብር አገኘሁ'ት ያለውን መሳሪያም በተመለከተ አንደኛው ከአባታቸው በውርስ ያገኙትና የማይሰራ መሆኑን፤ ሌላኛው በ1998 ዓ.ም ከመንግሥት የተቀበለው ሕጋዊ ፈቃድ ያለው መሳሪያ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረባቸውን አቶ ልደቱ እንደነገሯቸው፤ ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል።

የሚቆምላቸው ጠበቃ ባለማግኘታቸው እስካሁን በራሳቸው ሲከራከሩ የቆዩት አቶ ልደቱ፤ ዛሬ በጠበቃ እንደተከራከሩ አቶ አዳነ ጨምረው ተናግረዋል።

"አቶ ልደቱ ጠበቃ ማግኘት እንዳልቻሉ በየሚዲያው ከገለፅን በኋላ ባለፈው ሳምንት ኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኦሮምኛ ተናጋሪ ጠበቆች በነፃ እንቆምልሃለን ባሉት መሰረት ዛሬ የተከራከሩት ከአንድ ጠበቃ ጋር እየተመካከሩ ነው" ብለዋል።

አቶ ልደቱ በሚሰጠው ቀጠሮ ተስፋ የቆረጡ ሲሆን 'ድንገት ከምርጫው በኋላ፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው ልለቀቅ የምችለው እስከ ሁለት ዓመት ራሴን አዘጋጅቼ ነው ያለሁት' በማለት እንደነገሯቸው አቶ አዳነ አስረድተዋል።

አቶ አዳነ የጤና ሁኔታቸውም ዛሬ ፍርድ ቤት ከገቡ ጀምሮ ነስር በተደጋጋሚ እያስቸገራቸው እንደነበር ገልፀው፤ ሕክምና እንዲያደርጉ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ቢኖርም ፍርድ ቤቱ ባለመፍቀዱ አቶ ልደቱ "የሞት ፍርድ የተፈረደብኝ ያህል ነው የምቆጥረው" ማለታቸውን አክለዋል።

የፓርቲው ፕሬዚደንት አክለውም የሚመጣውን ውጤት ከመጠበቅ ውጭ በፍርድ ሂደቱ እኛም ተስፋ ቆርጠናል ብለዋል።

"እስሩ ፖለቲካዊ ነው" ያሉት አቶ አዳነ ጉዳዩን በንግግር ለመፍታት ከዚህ በፊት ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባታቸውንና ለመወያየት ጥረት አድርገው እንደነበር፤ ይሁን እንጅ ፍርድ ቤት የያዘው ጉዳይ ስለሆነ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉ እንደገለፁላቸው አስታውሰዋል።

አሁን ለመጨረሻ ጊዜ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ደብዳቤ ለመፃፍ መዘጋጀታቸውን አቶ አዳነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።