የአሜሪካ ምርጫ፡ ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ከሆኑ የሚለወጡ 8 ጉዳዮች

ዶ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጆ ባይደን በ2020 ለፕሬዝዳንትነት እወዳደራለሁ ሲሉ ሁለት ነገር ለማሳካት እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡

አገሪቱን መልሶ ለመገንባት እና በትራምፕ የተነሳ የተበታተነውን "ብሔራዊ መንፈስ" ወደ አንድ ለማማጣት፡፡

ከዚህ ባሻገር የሚከተሉት 8 ነጥቦች ባይደን ከተመረጡ የሚቀየሩ ጉዳዮች ይሆናሉ፡፡

1. ኮቪድ-19 ላይ ታላቅ ዘመቻ ይከፈታል

በአሜሪካ ከኮሮናቫይረስ የባሰ ወቅታዊ ጠላት የለም፡፡ ባይደን ለሁሉም ዜጎች ነጻ ምርመራ በፍጥነት እንዲደረግ ያደርጋሉ፡፡ መቶ ሺህ ሰዎች ደግሞ ይቀጠራሉ፡፡

የእነዚህ 100ሺህ ሰዎች ሥራ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እግር በእግር አድኖ ንክኪ ቀጠናቸውን መለየት ይሆናል፡፡ ‹መርምር-አድን› በሚለው ስልት የቫይረሱን ግስጋሴ ለማቆም ይሞከራል፡፡

በየግዛቱ 10 የምርመራ ማዕከላት ይከፈታሉ፡፡ ሁሉም የግዛት ገዢዎች ጭምብል ማድረግን ያስገድዳሉ፡፡ አሜሪካ በኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎቿ ሳይንሳዊ አካሄድ ቫይረሱን ድል ታደርጋለች ይላሉ፣ ባይደን፡፡

2. በሰዓት ዜጎች የሚከፈላቸው ትንሹ ምንዳ ከፍ ይላል

በኮሮና ምክንያት የተጎዱ ቢዝነሶች ዘለግ ባለ ጊዜ የሚመልሱት ብድር ይሰጣቸዋል፡፡

ለተቸገሩ ቤተሰቦች ወርሃዊ ክፍያ በቀጥታ ያገኛሉ፡፡ አሁን ከሚከፈለው በተጨማሪ 200 ዶላር ይሰጣል፡፡ የፌዴራል ትንሹ የሥራ ምንዳም በሰዓት ወደ 15 ዶላር ከፍ ይደረጋል፡፡

3. የፍትሕ ሥርዓቱ ማሻሻያዎች ይደረጉበታል

የጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ መገደሉን ተከትሎ ጥቁሮች ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡

ጆ ባይደን ቁጣችሁ ይገባኛል ብለዋቸዋል፡፡ ጆ በአሜሪካ ዘረኝነት እንደተንሰራፋ ያምናሉ፡፡ ይህን ማሻሻል የሚቻለው ግን የፍትህ ሥርዓቱን በማዘመን፣ የኅብረተሰብ አቀፍ ልማቶችን በማካሄድ ነው፡፡

ስለዚህ ‹ቢዩልድ-ባክ› እየተባለ በሚጠራው መርሐግብራቸው ጥቁር ድሃ ማኅበረሰብን መደገፍ፣ የተገለሉ አሜሪካዊያንን እድል መስጠት፣ ሥራ እንዲፈጥሩ፣ ቢዝነስ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያስባሉ፣ ባይደን፡፡

ለዚህ የሚሆን 30 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ አዘጋጃለሁ ብለዋል፡፡ የሞት ፍርድን ከማስቀረት ጀምሮ ፍርደኞችን ማንገላታት አስቆማለሁ፣ መብት አጎናጽፋቸዋለሁ፤ ፖሊስ የሚወስደውን ያልተመጣጠነ ኃይል ለማስቀረት ቃል እገባለሁ ብለዋል፣ ባይደን፡፡

4. ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ትብብር መድረክ ይመለሳሉ

ባይደን የአየር ንብረት ለውጥ ትልቁ የምድራችን ፈተና ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ትራምፕ ግን አሜሪካንን ለመጎተት ነው የአየር ንብረት ለውጥ ብሎ ነገር የለም፣ ‹‹ውሸት ነው›› ይላሉ፡፡

ዓለም ካልተባበረች ምድር ጭንቅ ውስጥ ትገባለች ብለው የሚያምኑት ጆ ባይደን በካይ ልቀትን ለመቀነስ እሰራለሁ ብለዋል፡፡ የፓሪስ ስምምነት አሜሪካ በ2025 የግሪንሀውስ ጋዝን በ28 ከመቶ እንድትቀንስ ይጠይቃል፡፡

የዚህ ስምምነት ፈራሚ የነበረችው አሜሪካ፣ በትራምፕ ውሳኔ ከስምምነቱ ወጥታለች፡፡ ባይደን እመለሳለሁ ብለዋል፡፡ለአረንጓዴና ታዳሽ ቴክኖሎጂዎች፣ ምርምሮችና ተያያዥ ሥራዎች 1.7 ትሪሊዮን ዶላር ለ10 ዓመት እመድባለሁ ይላሉ፣ ጆ፡፡

5. ከኔቶና ከቻይና ጋር ግንኙነት ያሻሽላሉ

ባይደን ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ችግሮች እሰጣለሁ ቢሉም የውጭ ፖሊሲያቸው ምን እንደሚመስል ከመናገር አልተቆጠቡም፡፡ ከኔቶ ጋር በትራምፕ ምክንያት የሻከረውን ግንኙነት እጠግናለሁ ብለዋል፡፡

ከቻይናም ጋር ቢሆን የንግድ ጦርነት ውስጥ ከመግባትና የአንድ ወገን የታሪፍ ጭማሪ ከማድረግ ቻይና ችላ ከማትላቸው ከሌሎች አገሮች ጋር የጎንዮሽ ጥምረት በመፍጠር ቻይናን ወደ መስመር አስገባታለሁ ብለዋል፣ ጆ፡፡ እነዚህ ቻይና ችላ የማትላቸው አገራት እነማን እንደሆኑ ግን በስም አልጠቀሱም፡፡

6. ኦባማኬር ይቀጥላል

ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ አለቃቸው ኦባማ ያስጀመሩት የጤና ኢንሹራንስ መድን መርሀግብር እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡

በዚህ የኢንሹራንስ ማዕቀፍ 97 ከመቶ አሜሪካዊያን ይታቀፋሉ ተብሎ ነበር የሚጠበቀው፡፡

ከኦባማኬር በተጨማሪ ሌሎች የጤና መድኅኖችን ለማካተትም ባይደን ይፈልጋሉ፡፡

7. የትራምፕን ፖሊሶዎች ይከልሳሉ

በመጀመርያዎቹ መቶ ቀናት እፈጽመዋለሁ ካሏቸው ነገሮች አንዱ ትረምፕ በሜክሲኮና በአሜሪካ ድንበር ጥገኝነት ጠየቂ ቤተሰቦችን የሚነጣጥለውን ፖሊሲ ቀዳድጄ እጥለዋለሁ ብለዋል፡፡

ይህ ፖሊሲ እናትና ልጅን ያለያየ ነበር ተብሎ ይተቻል፡፡ ከሙስሊም አገራት ወደ አሜሪካ የሚመጡ ሰዎችን የሚገድበውን ሕግ ለማንሳት ይፈልጋሉ ባይደን፡፡

በልጅነታቸው በሕግ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የመጡ ልጆችን (ድሪመርስ) ኦባማ ልዩ የመብት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አድርገው ነበር፡፡

ትራምፕ ግን ያን ሽረውት ቆይተዋል፡፡ ይህንን በአገሬው አጠራር ድሪመርስ የሚባሉትን የሕለመኛ ልጆችን ሕልም ማስቀጠል ይፈልጋሉ ባይደን፡፡ ይህም ለ‹‹ህልመኞቹ›› ትምህርት የመማር፣ ሥራ የማግኘት መብቶቻቸውን ማስጠበቅን ይጨምራል፡፡

8. የተማሪዎች የኮሌጅ ውዝፍ ብድር ይነሳል

ግራ ዘመም ናቸው ካስባላቸው የጆ ባይደን ሐሳቦች አንዱ ትምህር ፖሊሲ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ባይደን ለአመታት የተከማቸ የተማሪዎችን ውዝፍ ብድር መሰረዝ ይፈልጋሉ፡፡

የነጻ ትምህርት የሚሰጡ ኮሌጆችን ማስፋፋት ይሻሉ፡፡ ከመዋእለ ሕጻናት በፊት ባሉ የትምህርት ደረጃዎች ሁሉም ሕጻን ተቀራራቢና ወጥ ትምህርትን በነጻ የማዳረሱን ሐሳብ (Universal preschool) እንዲስፋፋ ይፈልጋሉ፡፡

ጆ ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ከየት ያመጣሉ ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ገንዘብ ከየት ያመጡታል ሲባል ዶናልድ ትራምፕ የታክስ ምሕረት ካደረጉላቸው ባለጸጎች ግብር ሰብስቤ ለዚህ ተግባር አውለዋለሁ ብለዋል፤ ጆ፡፡

ይህ ሁሉ የሚሳካው ግን ኅዳር 3 የዕድል ቀናቸው ከሆነች ብቻ ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካዊያንን ለሌላ አራት ዓመት ይሾፍራሉ፡፡