አሜሪካ፡ ለቻይና ሲሰልል ነበር የተባለው የሲአይኤ ባልደረባ ተያዘ

የሲአይኤ አርማ

የፎቶው ባለመብት, SAUL LOEB

ቀድሞ የሲአይኤ የደኅንነት መኮንን ነበር፡፡ ከሌላ የሩቅ ዘመዱ ከነበረ ሌላ የሲአይኤ አባል ጋር ተመሳጥሮ ለቻይና ሲሰልልና መረጃ ሲያቀብል ደርሼበታለሁ ብሏል፣ አቃቤ ሕግ፡፡

አሌክሳንደር ዩክ ቺንጋ ማ ይባላል ይህ ሰው፡፡ 67 ዓመቱ ነው፡፡ ባለፈው አርብ ነው በቁጥጥር ሥር እንዲውል የተደረገው፡፡

ከብሔራዊ ደኅንነትና መከላከያ ጋር የተያያዙ ከፍ ያሉ ምስጢራዊ ሰነዶችን ለቻይና አሳልፎ ይሰጥ ነበር ተብሏል፡፡

ዋሺንግተን እና ቤጂንግ ግንኙነታቸው እየሻከረ በመጣበት ጊዜ ነው አሌክሳንደር በቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡

አሌክሳንደር በሕጋዊ መንገድ የአሜሪካ ዜግነት ያገኘው ከአመታት በፊት ሲሆን ሲአይኤን የተላቀለው ግን በ1982 ዓ.ም ነበር፡፡

የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ለ7 ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል አገልግሎት ከሰጠ በኋላ በሰላም በመልቀቅ የተሰናበተ ሲሆን ከዚያ በኋላ በሻንጋይ መኖር ጀምሮ በ2001 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ደሴት ሀዋዩ ተመልሷል፡፡

አሌክሳንደርና በስም ያልተጠቀሰው ሌላ አንድ ዘመዱ ለረዥም ጊዜያት የሲአይኤን የውስጥ አሰራርና የሚወስዳቸውን ምስጢራዊ እርምጃዎች፣ አንዲሁም መረጃዎችን እንዴት እንደሚያጠፋ ዘርዘር ያለ ዶሴ ለቻይና ያቀብሉ ነበር ተብሏል፡፡

አሌክሳንደር ዛሬ ማክሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብና ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እድሜ ልክ ሊፈረድበት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ለምን እስከዛሬ አልተከሰሰም ታዲያ?

አሌክሳንደርና ሌላ ዘመዱ ሁለቱም ከሲአይኤ ከለቀቁ በኋላ በመጋቢት 2001 በሆንግኮንግ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን የሲአይኤን መረጃ ለቻይና አቀብለዋል ይላል የአቃቤ ሕግ ክስ፡፡

ያኔ ሁለቱ የቀድሞ የሲአይኤ መኮንኖችና ዘመዳሞች በተገናኙበት ወቅት የተነጋገሩት ነገር በከፊል በፊልም የተቀረጸ ሲሆን በፊልሙ ላይ አሌክሳንደር መረጃውን በማካፈሉ የተሰጠውን 50 ሺህ ዶላር ሲቆጥር ይታያል፡፡

ይህንን ፊልም ማን እንዴት አድርጎ እንደቀረጸው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

አሌክሳንደር ወደ አሜሪካ ደሴት ሐዋዩ ግዛት ከተመለሰ በኋላ በአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ውስጥ ሥራ ማመልከቱን አቃቢ ሕግ ጠቅሶ ይህንንም ያደረገው ለቻይና መረጃ ለማቀበል እንዲመቸው ነው ሲል ከሶታል፡፡

እንዳሰበውም ተሳክቶለት በኤፍቢአይ የሕዋዩ፣ የሆኑሉሉ ቢሮ በ2004 ሥራ ተቀጥሯል፡፡ በዚያን ወቅት ያገኛቸው የነበሩ መረጃዎችንም ለቻይና ያቀብል ነበር ተብሏል፡፡

ከአሌክሳንደር ጋር መረጃ ያቀባብል ነበር የተባለው ሌላኛው ዘመዱ አሁን 85 አመታቸው ሲሆን አቃቢ ሕግ በክሱ አላካተታቸውም፤ ይህም በጤና ምክንያት እንደሆነ ተገለጾ ታልፏል፡፡

አሌክሳንደር ለቻይና ይሰልል እንደነበረ ከታወቀ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ሆኖ ነገር ግን ለምን እስከዛሬ ተከሶ ለፍርድ እንዳልቀረበ ግልጽ አልተደረገም፡፡