ጣልያን፣ ቱኒዝያ ስደተኞችን እንድታስቆምላት 13 ሚሊዮን ዶላር ልትሰጥ ነው

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የጣልያን መንግሥት የሜድትራንያን ባህር አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን እንድታስቆምላት 13 ሚሊዮን ዶላር ለቱኒዝያ ለመስጠት መወሰኑ ተገልጿል።

በርካታ ስደተኞች በትናንሸ ጀልባዎች ሜድትራንያን ባህር አቋርጠው ወደ ጣልያን እንደሚያቀኑ የተገለፀ ሲሆን ይህ የገንዘብ ልገሳም ቱኒዝያ የባህር ድንበሯን ለማጠናከርና ስደተኞቹንም ለማስቆም ያለመ ነው።

የጣልያን መንግሥት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለማስቆምም የባህር ላይ ድንበሮችን ጥበቃ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ለቱኒዝያ መንግሥት መልእክት አስተላልፏል።

ይህንን የተናገሩት በቱኒዝ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉይጂ ዲ ማሪያ ናቸው።

ሚኒስትሩ በአገራቸው ውስጥ "በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው ለሚገቡ ስደተኞች" ቦታ የለም ብለዋል።

ስደተኞችን በየትኛውም መንገድ ለማስቆም እየሰራ ያለው የጣልያን መንግሥት የቱኒዝያን የባህርና ፀጥታ ኃይሎች ለማሰልጠንም ጠይቋል።

እነዚህም ሰልጣኞች ስራቸው ስደተኞች በባህር ሊሻገሩ ሲሉ አድኖ መያዝና በቁጥጥር ስር ማዋል ይሆናል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በየቀኑ የሚገቡባት ጣልያን ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብኛል እያለችም ትገኛለች።