ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መከላከያ ሚንስትርነትን ጨምሮ አዳዲስ ሹመቶችን ሰጡ

ታከለ ኡማ እና ለማ መገርሳ

የፎቶው ባለመብት, Tekele Uma Facebook Page/BBC

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዛሬው ዕለት አዳዲስ አስር ሹመቶችን ሰጥተዋል።

ከሰሞኑ ከኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ አባልነታቸው የታገዱት አቶ ለማ መገርሳ ከመከላከያ ሚነስትርነታቸው ተነስተዋል።

በአቶ ለማ ምትክ ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) የመከላከያ ሚንስትር ሆነው መሾማቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፌስቡክ ገፅ ከሰፈረው መረጃ መረዳት ተችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ ምትክ ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግነቱን ቦታ የተረከቡ ሲሆን፣ ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ መሾማቸውንም መረጃው ጠቁሟል።

ሌሎቹ ሹመቶች ተስፋዬ ዳባና ፍቃዱ ጸጋ በምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግነት፣ ዮሐንስ ቧያለው፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፣ እንደአወቅ አብቴ፤ የብረታ ብረት ኢንጅኔሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ ፕሮፌሰር ኂሩት ወልደ ማርያም፤ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ናቸው።

የጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት ቃለ አቀባይ የነበሩት አቶ ንጉሡ ጥላሁን ካሉበት ኃላፊነት ተነስተው የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሹመት እንደተሰጣቸውም መረጃው ጠቁሟል።

የሚኒስትሮቹ ሹመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ቀርቦም መፅደቅ ያለበት ሲሆን ፤ ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት እረፍት ላይ መሆኑም ይታወቃል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን አስመልክቶ ፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ማገልገል ደስታ እንደሰጣቸውና የከተማዋን ችግሮች ለመቅረፍ የተቻላቸውን ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

"አዲስ አበባን መምራት ትልቅ ዕድል ነው። ደጋግመን እንደምንለው፤ "በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን እድል" ላለማባከን ጥረናል። በሁሉም ውስጥ የነዋሪዎቻችን ብርቱ ድጋፍ አብሮን ነበር። አዲስ አበባን እንደስሟ ለማድረግ በደስታ፤ በፍላጎትና በፍቅር ስንተጋ ምርኩዝ ለሆናችሁን ሁሉ፤ ከልቤ አመሰግናለሁ! በፍጹም ቅንነት ላጎደልናቸው ነገሮችም ይቅርታ እጠይቃለሁ" በማለት መልዕክታቸውን አስፍረዋል።