አሜሪካ፡ ዘበኛ ሆኖ በሰራበት ሆስፒታል የሕክምና ትምህርት የጀመረው ጥቁር አሜሪካዊ

ረስል ሌዴት

የፎቶው ባለመብት, Submitted photo

የቀድሞው የሆስፒታል ዘበኛ ወደ ሆስፒታሉ ተመለሰ፡፡ ለጥበቃ ግን አይደለም፡፡ ሊታከምም አይደለም፡፡ ምናልባት ሊያክም ይሆናል፡፡ ለጊዜው የሕክምና ትምህርት ጀምሯል፡፡

እንዴት አሳካው?

የዛሬ 11 ዓመት ራስል ላዴት በባተን ሩዥ ሆስፒታል ጥበቃ ነበር፡፡

በዘበኝነት እየሠራ ታዲያ ከእጁ በትር ሳይሆን የጥናት ካርዶችን ነበር በብዛት ይዞ የሚታየው፡፡ ያን ጊዜ ኬሜስትሪ እየተማረ ነበር በትርፍ ሰዓቱ፡፡

አሁን ፒኤችዲ (PhD) ደርሷል፡፡ ሦስተኛ ዲግሪ፡፡ ቀጥሎ ኤምዲ የህክምና ዶክተሬቱን ለማግኘት እየተማረ ነው፡፡

የሚማረው በሉዊዚያና ቱሌን ዩኒቨርስቲ ነው፡፡

‹‹ሕልሜ እውን እየሆነ እንዳለ ይሰማኛል›› ብሏል ለቢቢሲ፡፡

አሁን እሱ ራሱ የብዙዎች መነጋገርያ እየሆነ እንደመጣ ገብቶታል፡፡ ድሮ ዘበኛ እያለ ዞር ብሎ የሚያየው ሰው እንኳ አልነበረም፡፡ እሱ ሌላውን ዞር ብሎ ያያል እንጂ፡፡ የሥራው ባህሪም ስለነበረ፡፡

ራስል ባለፈው ዓመት እንዲሁ በሌላ ነገር ስሙ ሲነሳ፣ ሲወሳ ነበር፡፡

በሊዊዚያና የባሪያ ፍንገላ መታሰቢያ ሙዝየም ውስጥ ግሩም የሆነ የፎቶ አውደ ርዕይ አሰናድቶ ነበር፡፡ የፎቶ አውደ ርዕዩ 15 ጥቁር ሴት የሕክምና ተማሪዎችን የያዘ ነበር፡፡

ይህ ሥራው በበይነ መረብ ድንገቴ ትኩረት አግኝቶ እንደ ሰደድ እሳት ተሰራጨ፡፡ ከፍተኛ ዝናና እውቅናን አስገኘለት፡፡

ይህን ተከትሎ ‹‹15 ዋይት ኮትስ›› የሚባል ድርጅት መሠረተ፡፡ የድርጅቱ ዓላማ ክፍያ መክፈል የማይችሉ ጥቁር አሜሪካዊያንን በፋይናንስ ማገዝ ነበር፡፡

ራስል በአውድ ርዕዩ ያቀረባቸውን ፎቶዎች ቅጂ በአሜሪካ ለሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ልኳል፡፡

ይህን ያደረገው ጥቁር ልጆችን ለማነቃቃት ነበር፡፡ የሚቀጥለው ጥቁር አሜሪካዊ ትውልድ በሽተኛ ሳይሆን ሐኪም በመሆን እንዲታወቅ ለማድረግ፡፡

‹‹አሁን ዝም ብለሽ ሄደሽ የሆኑ ሕጻናትን 'ሐኪም ማንን ይመስላል?' ብትያቸው፣ ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ነጭ ጋውን የለበሰ ነጭ ሰውዬ ነው›› የሚለው ራስል ይህንን ገጽታ ለመቀየር በሚል እሳቤ ፎቶዎችን ወደትምህርት ቤቶች እንደላካቸው ለቢቢሲ ዘጋቢ ነግሯታል፡፡.

የፎቶው ባለመብት, The 15 White Coats

እንዴት ከሆስፒታል ዘበኝነት ተነስቶ ሐኪም ሆነ?

ትንሽ ወደኋላ ሸርተት ብለን ልጅነቱን እንቃኝ…

ራስል በሌክ ቻርለስ፣ ሉዊዚያና ከእናቱ ጋር በድህነት ነበር ያደገው፡፡

እንኳንስ ፒኤችዲ ሊሰራ፣ እንኳንስ ኤምዲ ለማግኘት ሊማር ቀርቶ ዩኒቨርስቲ ደጅ እረግጣለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡

ራስል ሦስተኛው ዲግሪውን የሠራው በሞለኩዩላር ኦንኮሎጂ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ የሱን ልጅነት ለሚያውቅ ሰው አስደናቂ ነው፡፡

ልጅ ሳለ ራስል ትዝ የሚለው ሀብታሞች የጣሉትን ምግብ ለማግኘት ከእህቱ ጋር ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ትራፊ ሲፈልጉ ነው፡፡

‹‹እኔ ይመስለኝ የነበረው ሀብታሞች ብቻ የሚገቡበት ቦታ ነበር›› ይላል ድሮ ስለ ኮሌጅ የነበረውን ስሜት ለቢቢሲ ሲናገር፡፡

ልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲጨርስ አየር ኃይል ውስጥ ገባ፡፡ እንደማምለጫም፣ እንደ መደበቂያም…

‹‹ወታደር ቤት ያገኛቸው ሰዎች ጠንካሮች ነበሩ፡፡ ስኬት ለማንም ሰው የሚደረስበት ነገር እንደሆነ የተማርኩት በወታደር ቤት ነው›› ይላል፡፡

በዋሺንግተን ዲሲ በኋላም በፔንሳኮላ፣ ፍሎሪዳ በወታደራዊ ክሪፕቶሎጂ ቴክኒሻንነት ሰለጠነ፡፡

‹‹እየተማርኩ ስሄድ ዓለም ባለ ብዙ አማራጭ፣ ባለብዙ እድሎች እንደሆነችው እየገባኝ መጣ፡፡ እይታዬም ሰፋ፡፡››

በፔንሰኮላ ከተማ የወደፊት የትዳር አጋሩን አገኘ፡፡

የትደር አጋሩን ሲገልጻት፣ ‹‹በትምህርት እንዳምን ያደረገችኝ እሷ ናት፡፡›› ይላል፡፡

በአየር ኃይል ውስጥ በርከት ያሉ አገሮች እየተዟዟረ ከሰራ በኋላ ከሚስቱ ጋር የተረጋጋ ኑሮ ለመጀመር ሲል ከወታደር ቤት ራሱን አሰናበተ፡፡

ከ2009 ጀምሮ በበተን ሮዥ፣ ሊዊዚያና መኖር ጀመሩ፡፡

እሱ እዚያው ከተማ በሳውዘርን ዩኒቨርስቲ እና በኤም ኤንድ ኤም ኮሌጅ ተመዘገበ፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ተቋማት በቀደመው ጊዜ የሚታወቁት የጥቁሮች ትምህርት ቤት ሆነው ነው፡፡

ያን ጊዜ በነዚህ ኮሌጆች በስካላርሺፕ (ነፃ የትምህርት እድል አግኝቶ) ትምህርቱን እየተከታተለ የነበረ ቢሆንም ሙሉ ጊዜውን ለትምህርት ማዋል አይችልም ነበር፡፡

ማታ ማታ መሥራት ነበረበት፡፡ በዚያን ጊዜ ነበር የጥበቃ ሥራ በበተን ሮዥ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ ያገኘው፡፡

ቀን ቀን ይማርና ማታ ማታ ሆስፒታሉን ይጠብቃል፡፡ በዚያው መሀል ክፍተት ሲያገኝ የጥናት ካርዶቹን ያገላብጣል፡፡

ቅዳሜ ሲደርስ ደግሞ የጥበቃ ተራውን ለተረኛ ዘበኛ አስረክቦ ወደ ፔንሰኮላ ከተማ ይከንፋል፡፡ እዚያ ደግሞ ሌላ ሥራ አለው፡፡

በዚህ መሀል የመጀመርያ ልጁ ተወለደች፡፡

በዚህን ጊዜ ነበር ይበልጥ ጠንክሮ ከልሰራና የተሻለ ገቢ ማግኘት ካልጀመረ መጪው ጊዜ ለርሱም፣ ለሚስቱም፣ ለትንስዋ ልጁም ፈታኝ እንደሚሆን የተረዳው፡፡

ወደ ኒውዮርክ ሄዶ በሞሎኪውላር ኦንኮሎጂ ሦስተኛ ዲግሪውን ያዘ፡፡

‹‹ልክ ፒኤች ዲ መያዝ ስችል ምንም ነገር ማሳካት እንደምችል ተገለጠልኝ›› ይላል፡፡

ሁለተኛ ሴት ልጁ በየካቲት 20፣ 2018 ተወለደች፡፡

ይህ ሴት ልጁን ያገኘበት ዕለት ከቱሌን ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ‹‹ተቀብለንሀል!›› የተባለበት ቀን መሆኑ አስገረመው፡፡

ድሮ ጥበቃ ይሰራበት የነበረበት ትምህርት ቤት ሲመለስ የድሮ አለቃውን አመስግኗል፡፡ ‹‹በጥበቃ ሥራ ላይ ሳለሁ ተደብቄ ሳጠና አይቶኝ አላባረረኝም፡፡››

ራስል የሕክምና ትምህርቱን ሲጨርስ የሕፃናት ሕክምናና የአእምሮ ጤና ሕክምና ዘርፎች ለይ መሥራት ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ረገድ ጥቁር አሜሪካዊያንን መርዳት ይፈልጋልና፡፡

እሱ የተጓዘበት መንገድና ስኬት ድህነት እጣ ፈንታችን ነው ብለው እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡ አፍሪካ-አሜሪካዊ ወገኖቹን ያነቃቃል ብሎ ያምናል፡፡