የኢትዮጵያ መንግሥት ኤምባሲውን በተመለከተ ቅሬታውን አሰማ

የኢትዮጵያ ኤምባሲ

የፎቶው ባለመብት, SHUKRI JEMAL

የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባጋጠመው ክስተት አዲስ አበባ ውስጥ ላሉ የብሪታኒያ ኤምባሲ ከፍተኛ ባለስልጣን በይፋ ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ተገለጸ።

ይህ የሆነው በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደጅ ላይ ከሰሞኑ ለተቃውሞ በተሰበሰቡ ኢትዮጵያዊያን ሰልፈኞች የአገሪቱ ባንዲራ እንዲወርድ በመደረጉና በኤምባሲው ሠራተኛ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነው።

በዚህም ሳቢያ አምባሳደር ሬድዋን ኤምባሲው ላይ ስለተከሰተው ነገር በኢትዮጵያ የታላቋ ብሪታኒያና የዩናይትድ ኪንግደም ቻርጅ ዲ አፌር ለሆኑት አሌክስ ካሜሩን የመንግሥታቸውን ቅሬታ አቅርበዋል።

በዚህም ለንደን በሚገኘው ኤምባሲ ዙሪያ እየተከሰቱ ባሉ ጉዳዮችና የጽህፈት ቤቱን ደኅንነት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት የተሰማውን ቅሬታ ለኤምባሲው ባለስልጣን አሳውቀዋል።

ጨምረውም ዩናይትድ ኪንግደም በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የአገሪቱን ኤምባሲና ሠራተኞች ከየትኛውም አይነት ጣልቃ ገብነት መጠበቅ እንዳለባት አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይም የዩናይትድ ኪንግደም ቻርጅ ዲ አፌር አሌክስ ካሜሩን በኤምባሲው ላይ ስላጋጠመው ክስተት ይቅርታ መጠየቃቸውን ጠቅሶ፤ አገራቸው የኤምባሲውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ተገቢውን እርምጃ ትወስዳለች ማለታቸውን ገልጿል።

በኤምባሰው ደጅ ተሰባስበው ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩትን ከስፍራው እንዲሄዱ በፖሊስ በተደረገው ጥረት መካከል ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ በስፍራው የነበረ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በኤምባሲው ደጅ ተሰብስበው ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት ሰዎች በፖሊሶች ከቦታው ገለል እንዲሉ በተደረገው ጥረት ከተፈጠረ ግብግብ በኋላ በወቅቱ በፖሊስ የተያዙ መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ተቃዋሚዎቹ በኤምባሲው ደጅ ላይ በመሰባሰብ መንግሥትን የሚቃወም መፈክሮችን ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይም በኤምብሲው ህንጻ ላይ በመውጣት የአገሪቱን ባንዲራ አውርደው በሌላ ተክተዋል።

ለንደን የሚኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ሰኞ ዕለት "ተቃውሞ ለማሰማት የመጡ ጥቂት ሰልፈኞች በአንድ የኤምባሲው ሠራተኛ ላይ ድብደባ መፈጸማቸውንና የኤምባሲው አገልግሎት እንዲስተጓጎል መደረጉን" ገልጿል፡፡

ኤምባሲው አክሎም በአሁን ሰዓት ጥቃት የደረሰበት የኤምባሲው ሠራተኛ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝና ጥቃቱን የፈጸሙት ዜጎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አስታውቋል፡፡

ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የኤምባሲው ሰራተኛ በኤምባሲው ደጃፍ በተከሰተው ተቃውሞ ራሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የኤምባሲው ሠራተኞች ለደኅንነታቸው በመስጋት በቤታቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

ከዚህ ቀደምም ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ተቃዋሚዎች ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸው የሚታወስ ሲሆን አንድ ግለሰብ ላይም ጥቃት ተፈጽሞ ነበር።