አሜሪካ፡ ጥቁር አሜሪካዊው በ7 ጥይት መመታቱን ተከትሎ ተቃውሞ ተቀስቅሷል

ኬኖሻ ውስጥ ሕንጻዎችና መኪናዎች ተቃጥለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኬኖሻ ውስጥ ሕንጻዎችና መኪናዎች ተቃጥለዋል

ባለፈው እሁድ ዊስኮንሲን ውስጥ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ በጥይት መመታቱን ተከትሎ ተቃውሞ በርትቷል።

ፖሊስ፤ ጄኮብ ብሌክ የተሰኘውን የ29 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ ቢያንስ ሰባት ጊዜ በጥይት መቶታል ተብሏል።

ኬኖሻ የተባለችው በዊስኮንሲን ግዛት የምትገኘው ከተማ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ አተካራ መካከል ወደ መኪናው ሲገባ ፖሊስ አከታትሎ ሲተኩስበት የሚያሳይ ተንቃሳቃሽ ምስል ተሰራጭቷል።

ይህን ተከትሎ በግዛቲቱ ለሁለተኛ ቀን የዘለቀ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ሕንፃዎች ወድመዋል፤ መኪናዎች ተቃጥለዋል።

የግዛቲቱ አገረ ገዢ ቶኒ ኤቨርስ ብሔራዊው ክቡር ዘብ እንዲረዳቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው ግንቦት ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በአሰቃቂ ሁኔታ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ ለሳምንታት የዘለቀ ተቃውሞ አሜሪካን እንደናጣት አይዘነጋም።

ተቃዋሚዎች ፖሊስ ዜጎች በተለይ ጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚያደርሰውን በደል ያቁም ይላሉ።

የኬኖሻ ከተማ አስተዳደር ከምሽት 2 ሰዓት እስከ ጥዋት 1 ሰዓት የሚቆይ ሰዓት እላፊ ቢጥልም ተቃዋሚዎች ገደቡን ጥሰው ድምፃቸውን ሲያሰሙ አምሽተዋል።

በርካታ ወጣት ተቃዋሚዎች የከተዋማ ፍርድ ቤትን ሊጠብቁ ከቆሙ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። ተቃዋሚዎች 'ፍትህ ለጄኮብ' በማለት ድምፃቸውን እያሰሙ እንዳሉ ከሥፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ጄኮብ ብሌክ ቢያንስ ሰባት ጊዜ በጥይት ቢመታም በሕይወት እንዳለና ሕክምና እያገኘ እንደሆነ ተሰምቷል።

አገረ ገዢው ኤቨርስ "ብሔራዊው ክቡር ዘብን የጠራሁት ሰልፈኞች ድምፃቸውን ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲያሰሙና የሕዝብ ንብረት እንዳያወድሞ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ለተቃውሞ የወጡ ነዋሪዎች

ግለሰቡን በጥይት የመቱት ፖሊሶች በሕግ ጥላ ሥር ይዋሉ ያሉ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ወደ ከተማዋ ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ሰብረው ለመግባት ሙከራ አድርገዋል። ፖሊስ ይህን ለመከላከል አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

ዴሞክራቱ አገረ ገዢ ጥቁር አሜሪካዊው በፖሊስ በጥይት መመታቱን አውግዘዋል። ነገር ግን ይህ አስተያየታቸው ትችት አስከትሎባቸዋል።

የከተማዋ ፖሊስ ማኅበር ኃላፊ ፒት ዲተስ "አስተያየቱ ኃላፊነት የጎደለው ነው። ቢያንስ የተፈጠረው ነገር እስኪጣራ አስተያየት መስጠት አልነበረባቸውም" ሲሉ ይወቅሳሉ።

ሰውዬው በሁለቱ ነጭ ፖሊሶች ጥቃት ሲደርስበት የቀረፀው ግለሰብ ፖሊሶቹ ጥቁር አሜሪካዊውን በቡጢ እንደመቱት ለሲኤንኤን ተናግሯል።

ብሌክ ወደ መኪናው አቅንቶ በሩን ከፍቶ ዝቅ ሲልና አንዱ ነጭ ፖሊስ ካናቴራውን ይዞ አከታትሎ ሲተኩስበት በምስሉ ላይ ይታያል።

የዊስኮንሲን ፍትህ ቢሮ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ቢልም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የብሌክ አጋር የሆነችው ሴት ሦስት ልጆቻቸው መኪናው ውስጥ ከኋላ ተቀምጠው እንደነበርና አባታቸው በጥይት ሲመታ እንደተመለከቱ ተናግራለች።

የ29 ዓመቱ ግለሰብ ከቀዶ ህክምና ክፍል ወጥቶ አሁን በማገገሚያ ክፍል እንደሚገኝ ተዘግቧል።

ሰውዬው በጥይት መተዋል የተባሉት ሁለቱ ነጭ ፖሊስ የግዳጅ እረፍት ላይ ሲሆን እንዲከሰሱ ጥሪ እየቀረበ ነው።

ዴሞክራቱ ፕሬዝደንታዊ ዕጩ ጆ ባይደን የብሌክ ጉዳይ ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲጣራ ሲሉ ሰኞ መግለጫ አውጥተዋል።