ፖሊዮ፡ አፍሪካ ከ’ዋይልድ ፖሊዮ’ ነፃ መሆኗ ታወጀ

ክትባት ሲሰጥ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አፍሪካ ‘ዋይልድ ፖሊዮ’ ከሚባለው የፖሊዮ ቫይረስ ዝርያ ነፃ መሆኗን የሚያሳይ እውቅና ገለልተኛ ከሆነው የአፍሪካ የሰርቲፊኬት ኮሚሽን አገኘች።

የፖሊዮ ቫይረስ በአብዛኛው ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን የሚያጠቃ ሲሆን አንዳንዴ የነርቭ ሥርዓትን በመጉዳት ሊታከም የማይችል የአካል ጉዳት ያስከትላል።

የመተንፈሻ ጡንቻዎች በቫይረሱ ከተጎዱም ሞትን ያስከትላል።

በአፍሪካ ከ25 ዓመታት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት በቫይረሱ ሳቢያ የአካል ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

አሁን ይህ በሽታ የሚገኘው በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ውስጥ ብቻ ነው።

በሽታው መድኃኒት ባይኖረውም ክትባቱ ሕፃናትን እስከ እድሜ ልክ ድረስ ከቫይረሱ ይጠብቃቸዋል።

በአህጉሪቱ ከ’ዋይልድ ፖሊዮ’ ነፃ መሆኗን ያወጀችው የመጨረሻዋ አገር ናይጀሪያ ናት። በአገሪቷ በተካሄደው የክትባት ዘመቻ የፀጥታ ሁኔታቸው አስጊ የሆኑ ቦታዎችንና የገጠር አካባቢዎችን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረትን የጠየቀ ሲሆን፤ በዚህ ሂደትም የተወሰኑ የጤና ባለሙያዎችም በታጣቂዎች ተገድለዋል።

ፖሊዮ ምንድን ነው?

ፖሊዮ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ቫይረስ ነው። በአብዛኛው የሚተላለፈው በተበከለ ውሃ ነው።

ቫይረሱ የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት ለአካል ጉዳት ይዳርጋል።

ከ’ዋይልድ ፖሊዮ’ ሦስት ዝርያዎች ውስጥ ሁለቱ ከዓለም የጠፉ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ቀሪው ዝርያ ከአፍሪካ መጥፋቱ ተገልጿል።

ከ95 በመቶ በላይ የሆነው የአፍሪካ ሕዝብ ተከትቧል። ይህም የአፍሪካ የሰርተፊኬት ኮሚሽን አህጉሪቱ ከበሽታው ነፃ መሆኗን ከማወጁ በፊት ካስቀመጠው መለኪያ አንዱ ነበር።