ወሰንሰገድ ገብረኪዳን፡ "አዶኒስ አስካሁን ከሰራው በላይ ወደፊት ሊሰራ ያቀደው ነበር ያጓጓኝ"

አዶኒስ

የፎቶው ባለመብት, FB

በርካቶች አዶኒስ በሚለው ስሙ ያውቁታል። የገመና ቁጥር -1 እና የመለከት የቴሌቪዥን ድራማዎች ደራሲ እንዲሁም በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን የአና ማስታወሻን መጽሐፍ ተርጓሚው አድነው ወንድይራድ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል።

አዶኒስ ከነዚህ ሥራዎቹ በተጨማሪ የበርካታ መጽሐፍትን፣ የሕጻናት መዝሙሮችንና የበርካታ ፊልሞች፤ እንዲሁም የሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች ደራሲ እና ተርጓሚ ነው።

ብዙ ጊዜ ሚዲያዎች ላይ ቀርቦ ለመታየት ፍላጎት ያልበረው አዶኒስ በሙያው አርክቴክት [የሥነ ሕንጻ ባለሙያ] ነበር። በዚህም መስክ የበርካታ ሕንፃዎችን ዲዛይን እንደሰራ ይነገርለታል።

ለበርካታ ዓመታት በጓደኝነት ያሰላፈውና በርካታ የአዶኒስ ሥራዎችን በመተየብ የሚታወቀው የቀድሞው የኢትዮጵ ጋዜጣና መጽሔት ዋና አዘጋጅ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን አዶኒስ "ኪነ ጥበብን ማሳደግ አለብን" ብሎ ሙሉ ጊዜውን ለጥበብ የሰጠ ሰው ነበር ይላል።

ከ1993 ጀምሮ ከአዶኒስ ጋር እውቅና እንዳላቸው የሚናገረወው ወሰንሰገድ፤ አዶኒስ ከትርጉምና ከድርሰት ሥራዎቹ ባሻገርም ሠዓሊና የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋችም እንደነበር ይገልጻል።

አዶኒስ እስካሁን ከሰራቸው በላይ "ወደፊት ሊሰራ ያቀደው ነበር ይበልጥ ያጓጓኝ" የሚለው ወሰንሰገድ "ለአንድ ዓመት የተሰራ ተከታታይ ድራማ ሰርቶ ጨርሶ ነበር፤ ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ህፃናት ላይ መሰራት አለበት በሚልም ለህፃናት ራሱ ጊታር እየተጫወተ የሰራው መዝሙር ተጠናቆ ነበር፤ ይህንን ለሕዝብ ያበቃል ብዬ ስጠብቅ ነበር" ጓደኛው በድንገት መለየቱን መቀበል የተቸገረው ወሰንሰገድ።

ጓደኛ የነበረውን ተለየ ችሎታን በተመለከተም "ነገሮችን የሚያይበት የተለየ ገጽ ይገርመኝ ነበር። ውስብስብና ከባድ የሆነውን ነገር ቀለል አድርጎ የማቅረብ ችሎታው አስደናቂ ነበር፤ እምቅም ትልቅም ችሎታ ነበረው" ሲልም ለአዶኒስ ያለውን አድናቆት ይገልፃል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ከአዶኒስ ጋር ለወራት በአካል ተገናኝተው እንደማያውቁ የሚናገረው ወሰንሰገድ፤ ከአንድ ወር በፊት ደውሎለት "ይህ በሽታ ካልጠፋ ሳንተያይ ልንሞት ነው እንዴ?" እንዳለው በሐዘን ያስታውሳል።

እንደ ወሰንሰገድ ከሆነ አዶኒስ ከራስ ምታትና ነስር በስተቀር ሌላ የጤና እክል አልነበረበትም። ነገር ግን ከ15 ቀናት በፊት ህመም አጋጥሞት ምኒሊክ ሆስፒታል ገብቶ እንደነበር መስማቱን ይናገራል።

አዶኒስ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን የብዕር ስሙ - [አዶኒስ] የመጀመሪያ ወንድ ልጁ ስም ነው።

የአድነው ወንድይራድ (አዶኒስ) የቀብር ሥነ ሥርዓት ነሐሴ 20/2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ ተፈጽሟል።