ሩሲያ፡ "ቭላድሚር ፑቲን ተቃዋሚያቸው አሌክሴ ናቫልኒን አላስመረዙትም"

አሌክሴ ናቫልኒን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቭላድሚር ፑቲን ተቃዋሚያቸው አሌክሴ ናቫልኒን አስመርዘውታል የሚለውን ክስ የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ 'መሰረተ ቢስ' ብለውታል፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ክሱ ከእውነት የራቀ ከመሆኑም በላይ ከጉዳይ የምንጽፈውም እንኳን አይደለም ብለዋል፡፡

የጀርመን ሐኪሞች አሌክሴ እንደተመረዘ ፍንጭ መስጠታቸውን ተከትሎ ቃል አቀባዩ ለምን ለድምዳሜ አስቸኮላቸው ብለዋል፡፡

አሌክሴ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነበር ከቶምስክ ወደ ሞስኮ በአውሮፕላን በመብረር ላይ ሳለ ታሞ ራሱን የሳተው፡፡

በኋላ እሱ የተሳፈረበት አውሮፕላን ኦምስክ የተሰኘች የሩስያ ከተማ እንዲያርፍ ተደርጎ በሳይቤሪያ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ ሲያገኝ ቆይተዋል፡፡

ሆኖም ጀርመንና ፈረንሳይ የተሻለ ሕክምና እንደሚያደርጉለት በመሪዎቻቸው በኩል መግለጻቸውን ተከትሎ አሌክሴ ወደ በርሊን በአውሮፕላን አምቡላንስ ተወስዷል፡፡

አሁን ሕክምናውን እየተከታተለ የሚገኘውም በዕውቁ ሻርሌት ሆስፒታል ነው፡፡

አሁንም ድረስ ራሱን ስቶ የሚገኝ ቢሆንም ሐኪሞች ያለበት ሁኔታ ለስጋት አይሰጥም ብለዋል፡፡

የአሌክሴ ደጋፊዎች እንደሚገምቱት አውሮፕላን ከመሳፈሩ በፊት በዚያው በአየር ጣቢያ አንድ ካፌ ውስጥ ሻይ ሲጠጣ ነበር፤ የተመረዘውም ያን ጊዜ ነው፡፡

የሻርሌት ሆስፒታል ሐኪሞች አሌክሴ ሕይወቱ እንደሚተርፍ ቢናገሩም የጤና ጉዳት ከፍ ያለ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ መመረዙንም አረጋግጠዋል፡፡

የሩሲያ የታችችኛው ምክር ቤት አፈ ኡባኤ ቪያቼስላቭ ቮሎሲን አንድ ኮሚቴ የአሌክሴን ጉዳይ እንዲመረምር አዘዋል፡፡

ጉዳዩን እንዲመረመር ያዘዙት ግን ፑቲን አድርገውታል ወይ የሚለውን ለማጣራት ሳይሆን የውጭ ኃይሎች በሩሲያ ብጥብጥና አመጽ ለመቀስቀስ ያደረጉት ሳይሆን አይቀርም ከሚል ጠንካራ እሳቤ ተነስተው ነው፡፡

አሌክሴ አሁን 44 ዓመቱ ነው፡፡

በሩሲያ ገናና እየሆነ የመጣው የፑቲን ሰዎችን ሙስና በማጋለጡና አይነኬ የሚባሉትን ቭላድሚር ፑቲንን በመጋፈጡ ነበር፡፡

አሌክሴ ቭላድሚር ፑቲን የሚመሩትን ዩናይትድ ፓርቲ የተሰኘውን ገዥ ፓርቲ 'የሌቦችና ቀጣፊዎች መሸሸጊያ' ሲል ይጠራዋል፡፡

ለበርካታ ጊዜ ለእስር የተዳረገው አሌክሴ ፑቲንን ገፍቶ መቃወሙ ለሕይወቱ አስጊ እንደሚሆን ሲጠበቅ ነበር፡፡

በሩሲያ ተቃዋሚዎችን፣ የምርመራ ጋዜጠኞችን እና የሰብአዊ መብት አቀንቃኞችን የማፈን፣ የማሰር እንዲሁም የመመረዝ ሁኔታ በተደጋጋሚ ተከስቶ ያውቃል፡፡

ክሬምሊን በተለይም ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ ተቃዋሚዎችንና የቀድሞ ሰላዮችን፣ እንዲሁም ወደ ምዕራብ አገራት የከዱ ቁልፍ ዜጎቿን በመርዝ ኤጀንት እንደምትመርዝ የቅርብ ጊዜ ታሪኮች ይመሰክራሉ፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ‹ይሄ ቀልድ ነው፤ እኛ የምር አድርገንም አንወስደውም› ሲሉ መልሰዋል፡፡

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንግላ ሜርክል ባለፈው ሰኞ ሩሲያ የአሌክሴን ጉዳይ በገለልተኛ አካል እንድታጣራ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

ዩናይትድ ኪንግደምም በተመሳሳይ ግልጽና ተአማኒ ምርመራ ይደረግ ብላለች፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ሚስተር ፔስኮቭ ግን ምርመራ የምንጀምረው መጀመርያ አሌክሴ መመረዙን ስናረጋግጥ ነው፡፡ መቼ ተመረዘና ? ብለዋል፡፡