እግር ኳስ፡ ሊዮኔል ሜሲ 'የልቀቁኝ ደብዳቤ' ለባርሴሎና አስገባ

ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ እንቁ ሊዮኔል ሜሲ የልቀቁኝ ደብዳቤ ለባርሴሎና ኃላፊዎች ማስረከቡ ተነገሯል።

የ33 ዓመቱ የባርሴሎና ኮከብ አጥቂ ባለፈው ማክሰኞ የልቀቁኝ ማመልከቻ የተተየበበት ፋክስ ልኳል፤ በደብዳቤውም በዚህ የዝውውር መስኮት ባርሴሎናን መልቀቅ እንደሚፈልግ አሳውቋል።

ባርሴሎና በቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ባየርን ሚዩኒክን ገጥሞ 8-2 መረታቱ ይታወሳል።

የባለን ደኦር [የዓለም ኮከብ ተጫዋች] ሽልማትን ስድስት ጊዜ ማንሳት የቻለው ሜሲ ለስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ከፈረንጆቹ 2004 ጀምሮ ተጫውቷል። የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አራት ጊዜ ማንሳትም ችሏል።

ሜሲ ከባርሴሎና ጋር የገባው ውል የሚያበቃው በቀጣዩ ዓመት [2021] ነው። ከዚያ በፊት ተጫዋቹን መግዛት የፈለገ ክለብ 700 ሚሊየን ዩሮ ማውጣት ይኖርበታል።

ሜሲ ግን ስምምነቱ ላይ 'ካሻሁ በነፃ እንድሰናበት የሚያትት አንቀፅ አለ፤ እሱን ተግባራዊ ማድረግ እፈልጋለሁ' ብሏል።

የክለቡ ቦርድ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋሉ እየተባለ ነው። ሜሲ የክለቡ ፕሬዝደንት ጆሴፕ ማርያ ባርቶሜዩ ካልተሰናበቱ እንደማይቆይ ቢነገርም ተጫዋቹ ክለቡን ለመልቀቅ የቆረጠ ይመስላል።

ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ የባርሳ ደጋፊዎች ኑ ካምፕ ስታድየም ተሰብስበው በክለቡ ቦርድ አባላት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል።

ሜሲና ባርሴሎና ጉዳያቸውን በሕግ ፊት ሊፈቱ ይችላሉ እየተባለ ነው።

ስምምነቱ ላይ ሜሲ የልቀቁኝ ደብዳቤ ከሰኔ አስቀድሞ ካስገባ በነፃ ወዲያውኑ ሊለቅ ይችላል የሚል አንቀፅ አለ። ነገር ግን ይህ ቀን አልፏል።

ሜሲና ወኪሎቹ ግን የዘንድሮው ዓመት ውድድር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ስለተራዘመ አንቀፁ አሁንም ተግባራዊ መሆን አለበት ይላሉ።

ነገር ግን የሕግ ባለሙያዎች ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከሄደ ባርሴሎና የተሻለ ተጠቃሚ ነው ይላሉ።

ሜሲ ባርሴሎናን መልቀቅ የፈለገው በተለያዩ ምክንያቶች ነው ይላል ስፔናዊው ፀሐፊ ጉለም ባላግ። አንደኛው ምክንያት ከሰሞኑ የተከናነቡት ሽንፈት ነው። ነገር ግን ክለቡ ሜሲ እንዲለቅ ይፈልጋል ሲል ጉለም ይፅፋል።

ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎናን የተቀላቀለው የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር። ሜሲ ለዋናው ክለብ 731 ጊዜ ተሰልፎ 634 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

10 የላ ሊጋ ዋንጫ ጨምሮ 34 ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።