"ሴቶች ከወገብ በላይ ራቁታቸውን ቢሆኑ ምንድነው ችግሩ" የፈረንሳይ አገር ውስጥ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን

"ሴቶች ከወገብ በላይ ራቁታቸውን ቢሆኑ ምንድነው ችግሩ" የፈረንሳይ አገር ውስጥ ሚኒስትር

በበጋው ጊዜ በባሕር ዳርቻ ሆኖ ዘለግ ላለ ሰዓት ፀሐይ መሞቅ በምዕራብ አገራት የተለመደ ነው፡፡

በተለይም በስፔን፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ከወገብ በላይ እርቃናቸውን ሆነው ፀሐይ ይሞቃሉ፡፡

ሰሞኑን ፖሊስ በእንዲህ ያሉ ቦታዎች ፀሐይ እየሞቁ የነበሩ ጥቂት ሴቶችን "እስኪ ሸፈን አድርጉት" ብለው በመናገራቸው ከፍተኛ ውግዘት እየደረሰባቸው ነው፡፡

ጉዳዩንም የፈረንሳይ ማኅበራዊ ድራምባዎች እያራገቡት ሰንብተው የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ጋር ደርሷል፡፡

ሴቶቹ ፀሐይ እየሞቁ የነበረው ሴትን ሜሪ ላ ሜር ተብሎ በሚጠራው የባሕር ዳርቻ ላይ ነበር፡፡

ሦስት ፖሊሶች እነዚህ ከወገብ በላይ ጡት መያዣ እንኳን ለአመል ያህል ጣል ያላደረጉትን ሴቶች ደረታቸውን እንዲሸፍኑ ሐሳብ አቅርበውላቸዋል፡፡

ሴቶቹም ይህንን ለማድረግ እንደማይገደዱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ነገሩ የተጋጋለውም ከዚህ በኋላ ነበር፡፡

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚኒስትር "ፖሊስ ምን ነካው" ካሉ በኋላ ከእንዲህ ዓይነት ተንኳሽ ድርጊቱ እንዲቆጠብ መክረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከወገብ በላይ ራቁት መሆን አትችሉም ብለው በተናገሩት ፖሊሶች ላይ በመብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ውርጅብኝ ደርሶባቸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ጄራልድ ዳርማኒን ይህንኑ ተከትሎ በትዊተር ሰሌዳቸው "ነጻነት አንጡራ ሀብት ናት" ሲሉ ጽፈዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ሚኒስትሩ ፖሊስ በባሕር ዳርቻ ያሉ ሴቶችን "ጡታችሁን ሸፍኑ' ብሎ መጠየቁ መብት ገፈፋ ከመሆኑም በላይ አሳፋሪም፣ ነውርም ነው ብለዋል፡፡

ፖሊስ ሴቶቹን ደረታቸው እንዲሸፈን ጥያቄ ለማቅረብ የተደፋፈረው ባለፈው ሳምንት በባሕር ዳርቻው የነበሩና ልጆችን ይዘው እየተዝናኑ የነበሩ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ሲሉ ፖሊስ ሴቶቹ ደረታቸው ላይ አንድ ነገር ጣል እንዲያደርጉ ጥቆማ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነበር፡፡

ፖሊስ ድርጊቱን የፈጸምኩት ራቁት መሆን በሴንት ሜሪ ላ ሜር የባሕር ዳርቻ ክልክል ሆኖ ሳይሆን በቦታው ልጆችን የያዙ ቤተሰቦች ጥያቄ ስላቀረቡልኝ ነው ሲል ይቅርታ ጠይቋል፡፡

የፖሊስ ቃል አቀባይ ሌ/ኮሎኔል ማዲ ሴቶቹን ጡታቸውን ሸፈን እንዲያደርጉ የጠየቁትን ፖሊሶችን ወቅሰዋል፡፡

"እኔን በዩኒፎርም የምታዩኝ ሥራ ቦታ ነው" ሲሉም እሳቸውም በባሕር ዳርቻዎች ከደረት በላይ ራቁት ሆነው ፀሐይ እንደሚሞቁ ጠቁመዋል፡፡

በፈረንሳይ በባሕር ዳርቻዎች ከደረት በላይ ራቁት ሆኖ ፀሐይ መሞቅ ሕገ ወጥ ድርጊት አይደለም፡፡ ሆኖም አንዳንድ የግዛት አካባቢዎች ይህንን ሊከለክሉ የሚችሉ ደንቦቸን እንደየሁኔታው ሊያወጡ ይችላሉ፡፡