ኮሮናቫይረስ፡ ዝነኛው ኬኤፍሲ ‹ጣት ያስቆረጥማል› የሚለውን ማስታወቂያ ከ70 ዓመታት በኋላ አቋረጠ

ዓለም አቀፉ የፈጣን ምግቦች አቅራቢ ኬኤፍሲ

የፎቶው ባለመብት, KFC

ዓለም አቀፉ የፈጣን ምግቦች አቅራቢ ኬኤፍሲ (KFC) ዝነኛ የሆነበትን የንግድ ማስታወቂያ ለማቆም ተገዷል፡፡

ማስታወቂያው ‹‹እጅ ያስቆረጥማል›› ("Finger Lickin' Good") የሚል ነበር፡፡

ይህ ማስታወቂያ ላለፉት 70 ዓመታት ለድርጅቱ እንደ መለያ ሆኖ አገልግሏል፡፡

የማስታወቂያው ጭብጥ ከወቅቱ ወረርሽኝ ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ቢቀር ይሻላል ተብሎ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡

"ድንገት ራሳችንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አገኘነው፤ ማስታወቂያችን እጅግ ተወዳጅ ነው፤ ግን ደግሞ ከጊዜው ጋር አልስማማ አለ፣ ምን ይደረግ?" ብሏል ኩባንያው፡፡

አሁን የዶሮ በርገርና የፒዛ ትእዛዞችን የሚያሽግበት ካርቶን 'የማይነበብ' ፅሑፍ የያዘ ሲሆን በቅርቡ አዲሱ የማስታወቂያ መሪ ቃሉ ምን እንደሚል ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን ብሏል፣ ኬኤፍሲ፡፡

ብዙዎቹ የኬኤፍሲ ቅርንጫፎች ከመጋቢት ወዲህ ዝግ ተደርገው የቆዩ ሲሆን አሁን ግን ቀስ በቀስ ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው፡፡

ድርጅቱ በዩትዩብ ላይ ባሰራጨው አንድ ቪዲዮ "ያ! 'እጅ ያስቆረጥማል የምንላችሁ' ነገር ለጊዜው ተውት" ይላል፡፡

አንዳንድ ሰዎች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በሰጡት አስተያየት፣ ድርጅቱ ዝም ብሎ ነው የሚዘባርቀው፣ ማስታወቂያው ከጤና ጋር አይጣረስም፡፡ ዞሮ ዞሮ ሰው በእጁ ነው የሚበላው፤ 'እጅ አትላሱ' ማለት ትርጉም አይሰጥም ብለዋል፡፡

ጣት ያስቆረጥማል የሚለው መልእክት በድርጅቱ ማስታወቂያ ላይ መሆኑ ለኮሮና ስጋት ነው የሚሉ ሰዎች በበኩላቸው ለሚመለከተው ባለሥልጣን ጥቆማ ከሰጡ በኋላ ነው ድርጅቱ አዲስ የማስታወቂያ ሐሳብ ለመጠንሰስ የተነሳው፡፡

163 ሰዎች ለአሜሪካ የማስታወቂያ ቁጥጥር ባለሥልጣን በሰጡት ጥቆማ እንዳሉት ኬኤፍሲ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው የፈጸመው፡፡

ወረርሽኙ እየተስፋፋ ‹ጣት የሚልሱ› ሰዎችን በቲቪ ማሳየት አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡

ኬኤፍሲ በ1930ዎቹ በኮሎኔል ሀርላንድ ሳንደርስ የተመሰረተ ዕድሜ ጠገብ የፈጣን ምግብ አቅራቢ ድርጅት ነው፡፡

ይህንን ‹እጅ የመላሱን› ማስታወቂያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሲጠቀምበት ቆይቶ በ1990ዎቹ እንዲቀየር ካደረገው በኋላ የዛሬ 12 ገደማ በድጋሚ በሥራ ላይ አውሎታል፡፡

ኬኤፍሲ በዓለም ላይ አሁን 22 ሺህ 500 ቅርንጫፎች አሉት፡፡

ከነዚህ ውስጥ 900 የሚሆኑት በዩናይትድ ኪንግደም ነው የሚገኙት፡፡ የድርጅቱ ባለቤት 'ያም ብራንድስ' ሲሆን ፒዛ ሐትን በባለቤት የያዘው ድርጅቱ ነው፡፡