የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን፡ "የመንግሥት ባለሥልጣናት ኃላፊነታቸውን በወቅቱ እና በብቃት አልተወጡም"

ብፁዕ ወቅዱስ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ማትያስ

ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በአንዳንድ ቦታዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባደረገችው ማጣራት እንደተረዳች አስታወቀች።

ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንን በማስመለክት ባወጣችው መግለጫ ላይ እንዳመለከተችው ድርጊቱን በማስቆምና ከተፈጸመም በኋላ ተጎጂዎችን በመካስና ፍትሕ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል የመንግሥት ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ስትል ወቅሳለች።

ይህንን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያቀረበችው ቅሬታ የክልሉ ያለበትን ተጨባጭ እውነታ ያላገናዘበና እየተደረገ ያለውን ጥረት ከግምት ያላስገባ ነው ሲሉ ለቀረበው ወቀሳ ለቢቢሲ መልስ ሰጥተዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ ያወጣችው መግለጫ 'በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ ዞኖች ተቀነባብረው በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጎዱ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናንን መርዳትና መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ' የወጣ እንደሆነ ያመለከተ ሲሆን፤ በሃጫሉ ሁንዴሳ ድንገተኛ ሞት ሐዘን እንደተሰማትም ገልጿል።

"ሆኖም በግድያው የተሰማትን ሐዘን ለመወጣት ጊዜ ሳይሰጣት፣ ሐዘንተኛነቷ ተረስቶ እና እንደ ጠላት ተቆጥራ፣ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በክርስቲያን ልጆቿ ላይ ዘግናኝ ፍጅት እና መከራ ተፈፅሞባቸዋል" ሲል መግጫው በመዕእመናን ላይ ደርሷል ያለውን ጉዳት አመልክቷል።

የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በእምነታቸው ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ፣ እንደተደፈሩና ቤት ንብረታቸው እንደወደመ ቤተ ክርስትያኗ በመግለጫዋ አትታለች።

"ብዙዎች ከሞቀ ቀዬአቸው ተፈናቅለው የክረምቱን ጨለማ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ መቃብር ቤቶች እና አዳራሾች፣ በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም በግሰለቦች ቤት ተጠልለው ለማሳለፍ ተገደዱ፤ ለአስከፊ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ቀውሶች ተዳረጉ" ሲል መግለጫው ያስቀምጣል።

ቤተ ክርስትያኗ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፍትህን በማስከበር ረገድ ተገቢውን እርምጃ አልወሰዱም ስትልም ትወቅሳለች።

"ቤተ ክርስቲያናችን፣ ይህንኑ የተቀነባበረ ጥቃት እንደሰማች፣ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በቋሚ ሲኖዶስ በኩል የሐዘን መግለጫ አውጥታለች፤ በአገር ውስጥ እና በውጭ በሐዘንና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስታመለክት ከርማለች" በማለት ከመጀመሪያው አንስቶ የተደረገውን ተግባር ጠቅሷል።

መግለጫው አክሎም "የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም "አጥፊዎችን አንታገሥም፤ ተገቢውን ፍትሕ እንሰጣለን፤ የተጎዱትን እንክሳለን፤" ብለው ቃል የገቡትን ይፈጽሙ እንደ ኾነ በማለት በትዕግሥት ጠብቃ ነበር።

"ሆኖም ዜጎችን ከጥቃት አስቀድሞ የመከላከል እና የመጠበቅ፣ ፍትሕን የማስፈንና ተጎጂዎችን በአግባቡ የመካስ ሐላፊነታቸውን በወቅቱ እና በብቃት ሲወጡ አላየችም" በማለት ወቅሷል።መግለጫው እንደተመለከተው ሲኖዶሱ በምዕመናን ላይ የደረሰውን ጉዳይ የሚያጠና ዐቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲቋቋም መመሪያ ሰጥቷል። ኮሚቴው ተጎጂዎችን፤ በጊዜያዊነት ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚሠራ ይሆናል።

ኮሚቴው በመጀመሪያ ዙር ሥራው ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች በዝርዝር በመለየት፣ ተጎጂዎችን የማጽናናት እና መረጃ የማሰባሰብ ጉዞ ማካሄዱ ተሰምቷል።

"የዐቢይ ኮሚቴው ልኡካን፣ ተጎጂዎችንና በማነጋገር እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የልጃችን የኃይለ ገብርኤልን [ሃጫሉ ሁንዴሳ] ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ የመንግሥትን መዋቅር ተገን ያደረጉ የእምነት እና የብሔር ጽንፈኞች አስቀድመው ከተደራጁ ኃይሎች ጋራ በመቀናጀት የፈጸሙት ስልታዊ እና አረመኔያዊ ጥቃት ዋና ዒላማ፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እንደነበሩ ተረጋግጧል» ይላል የሲኖዶሱ መግለጫ።

መግለጫው አክሎ ጉዳት ደረሰባቸው ያላቸውን ሰዎች ቁጥር ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሠረት ከሰኔ 22 ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት በተፈጸመው በዚያ ጥቃት ከ67 በላይ ምእመናን በግፍ እና በአሠቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፤ 38 ምእመናን ከባድ፣ 29 ምእመናን ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው መግለጫው አመልክቷል።

ከሰባት ሺህ በላይ ምእመናን ከመኖሪያቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር፣ በተለያየ ደረጃ ለሚገለጽ ሥነ ልቡናዊ እና ሥነ አእምሯዊ ቀውስ ተዳርገዋል፤ ከአምስት ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸውንም በዘረፋ እና በቃጠሎ ማጣታቸውን፣ ከዐቢይ ኮሚቴው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል» ብሏል።

ዐቢይ ኮሚቴው መንግሥት ችግር ያሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን መልሶ ለሟቋቋም ሊያደርጋቸው ይገባል ያላቸውን ተግባራት በዝርዝር አስቀምጧል።

«የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት፣ የኦርቶዶክሳውያን ኢትዮጵያውያንን በሕይወት የመኖር እና ሀብት የማፍራት ሰብአዊ እና ዜግነታዊ መብቶችን በማስከበር፣ የደኅንነት እና የኑሮ ዋስትና በአፋጣኝ እንዲያረጋግጥላቸው ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች።»

መንግሥት፤ 'ጥቃቱን ያቀዱትን፣ የፈጸሙትንና ያስተባበሩትን ኀይሎች እንዲሁም፣ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ወደ ጎን በማለት ጥቃቱን በዝምታ የተመለከቱትን በመዋቅሩ ውስጥ ያሉትን ሹማምንት እና የጸጥታ አካላት የኾኑ አጥፊዎችን፣ በቁጥጥር ሥር እንዲያውል' መግለጫው ጠይቋል።

በጥቃቱ እጃቸው የሌለ ምእመናን ከእሥር እንዲለቀቁም ቤተ ክርስትያኗ በመግለጫዋ አትታተለች።

«በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ አብዝቶ እንደሚነገረው፣ "በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ" ተብለው ብቻ የሚታለፉ አይደሉም» ትላለች ቤተ ክርስትያኗ።

ቤተ ክርስትያኗ አገር ቤትና ውጭ ሃገር የሚገኙ ኢትዮያውን ተጎጂዎችን ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቅርባለች።

ቤተክርስቲያኗ ያወጣችውን መግለጫ በተመለከተ ለቢቢሲ ምላሽ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ኮምኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የቀረበው ቅሬታ የክልሉን መንግሥት አይመለከትም በማለት "ተጎጂዎችን ወደ ማቋቋም የምንገባው በብሔር ወይንም በሐይማኖታቸው ሳይሆን ሰው በመሆናቸው ወይንም የክልላችን ነዋሪ በመሆናቸው" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያወጣችው መግለጫ የክልሉን እውነታ ያላረጋገጠ እና ክልሉ እየሰራ ያለውን እንዲሁም አሁንም ያለበትን ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ከሆነ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ በቤተክርስቲያኒቱም ሆነ ከቤተክርስትያኒቱ ውጪ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ውይይቶች በተለያየ ጊዜያት መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በኦሮሚያ የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ተከትሎ ግጭቱን የሐይማኖትና የብሔር መልክ ለማስያዝ የተሞከረበት ሁኔታ እንደነበር አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንን ክስተት የክልሉ መንግሥት በቁጥጥር ስር እንዳዋለውና የፀጥታ አካላትም በትኩረት መስራታቸውን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው አጥፊዎችን ወደ ሕግ እያቀረቡ መሆናቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።

የሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ከ150 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት እንደጠፋ ተዘግቧል።

በተጨማሪም ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቤት ንብረታቸው ወድሞ ለችግር መጋለጣቸውን የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ከሳምንታት በፊት ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ 523 መኖሪያ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን 499 መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው፤ በተጨማሪም 195 ሆቴሎች መቃጠላቸውን ሌሎች 32 ሆቴሎች ደግሞ በንብረታቸው ላይ የመሰባበር ጉዳት መድረሱን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

ከሁከቱ ጋር ተያይዞም በሺህዎች የሚቆተሩ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው መነገሩ ይታወሳል።