አሜሪካ፡ የጃኮብን ጥቃት በመቃወም የወጡ ሦስት አሜሪካዊያን ተገደሉ

ጃኮብ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ተቃውሞ እስካሁን ሦስት ሰዎች ተገድለዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጥቁር አሜሪካዊው ጃኮብ በፖሊሶች በደረሰበት ተኩስ ሆስፒታል ከገባ በኋላ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ሰዎች ሞተዋል፡፡

ሦስተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ተቃውሞ እስካሁን ሦስት ሰዎች ተገድለዋል፡፡

በአሜሪካ ዊስኮንሰን ግዛት፣ ኬኖሻ ከተማ ነበር ባለፈው እሑድ ወጣቱ በፖሊሶች የተተኮሰበት፡፡

የኬኖሻ የፖሊስ አዛዥ ዴቪድ ቤዝ ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት ከሆነ ግን እስካሁን በተቃውሞው የሞተ ሰው የሚያውቁት አንድ ሰው እንደሆነ ነው፡፡

ሰዎቹ የተገደሉት ተቃዋሚዎች ከልዩ ኃይሉ ጋር በተጋጩበት ጊዜ ነው፡፡

ጃኮብ ብሌክ የተባለ የ29 ዓመት ወጣት በፖሊስ የተተኮሰበት እሑድ እለት ነበር፡፡

ጃኮብ ወደ መኪናው ሲገባ ነበር ከኋላው በቅርብ ርቀት በሁለት ፖሊሶች ሲተኮስበት የነበረው፡፡

ጃኮብ በፖሊስ ሲተኮስበት የሚያሳየው ቪዲዮ ወደ በይነ መረብ ደርሶ ከተዛመተ በኋላ ልክ በግንቦት ወር የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ የተከሰተው ዓይነት መጠነ ሰፊ ተቃውሞ እንዳያገረሽ በሚል በአሜሪካ በብዙ ከተሞች ፖሊስ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

የዊስኮንሰን አገረ ገዥ ልዩ ኃይል ወደ ከተማዋ እንዲገባ ማዘዛቸው ይታወሳል፡፡

ጃኮብ ሲተኮስበት የሚያሳየው ቪዲዮ በተለቀቀ በሰዓታት ውስጥ ነበር በርካታ አሜሪካዊ የኬኖሻ ነዋሪዎች የከተማውን የፖለስ ጣቢያ የተቆጣጠሩት፡፡

ተቃውሞ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣቱ በርካታ መኪናዎች ወድመዋል፡፡ ፖሊስ የንግድ ሱቆች በአስቸኳይ እንዲዘጉ አድርጓል፡፡

ይህ የሆነው በከተማዋ የተደራጀ ዘረፋ በመስፋፋቱ ነው ተብሏል፡፡

በኬኖሻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታውጇል፡፡ ተቃውሞው አሁን ወደ ፖርትላንድ፣ ኦሬጎን፣ ሚኒሶታና ሌሎች ቦታዎች እየተስፋፋ ነው፡፡

ጃኮብ በተተኮሱበት ሰባት ጥይቶች የተነሳ ሕይወቱ ባታልፍም ከእንግዲህ ቆሞ ለመሄድ የሚያስችለው ሁኔታ እንደሌለው መዘገቡ ይታወሳል፡፡