ሳዑዲ አረቢያ፡ የዓለም መነጋገሪያ የሆነው የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ በሳዑዲ እስር ቤቶች

ጠባብ ቦታ ላይ የሚገኙት ስደተኞች
የምስሉ መግለጫ,

ጠባብ ቦታ ላይ የሚገኙት ስደተኞች በእንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ይናገራሉ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁለት ዓመታት በሹፌርነት ሲሰራ የነበረው *አብዱ በርካታ ልጆች ካሉበት ቤተሰብ እንደመጣ ይናገራል። የተሻለ ገቢ በማግኘት እናትና አባቱን እንዲሁም እህት ወንድሞቹን ለመደገፍ ነበር ከጓደኞቹ ጋር በጂቡቲ በኩል ባሕር አቋርጦ ወደ የመን ከወራት በፊት ያቀናው።

አብዱ ከጂቡቲ ተነስቶ ባሕሩን ለማቋረጥ 25 ሺህ ብር ሲከፍል፤ የመን ከደረሱ በኋላ ደግሞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር ሦስት ሺህ አምስት መቶ ሪያል [35 ሺህ ብር ገደማ] ከፍሏል።

በአንዲት ጀልባ 180 ሰዎች ታጭቀው በአደጋ መካከል ለ9 ሰዓታት፣ በአደገኛው ባሕር ላይ ተጉዘው ወደ የመን መግባት ችለው ነበር።

በጭንቅ ውስጥ ሆነው ባሕሩን እንዳቋረጡ የሚናገረው አብዱ ለአስራ አምስት ቀናት የመን ተቀምጠው በጦርነቱና በበሽታው መካከል መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቆይተዋል።

እቅዳቸው ወደ የመን ተሻግረው ከዚያም ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቋረጥ ሥራ አግኝቶ ያሰቡትን ማሳካት የነበረ ቢሆንም፣ በመካከል ላይ ኮሮናቫይረስ ተከስቶ የሁሉም ስጋት ሆነ። በዚህም እንኳን ከአገር ወደ አገር ማቋረጥ ቀርቶ በቆዩበት ጦርነት በሚካሄድባት የመን አማጺያኑ ወረርሽኙን ታስፋፋላችሁ በሚል እንዳሳደዷቸው ይናገራል።

የሁቲ አማጺያን አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ጫና ሲያሳድሩባቸው እንዲሁም በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት እዚያው የመን ውስጥ ህይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዳሉም ነግሮናል።

ለጥቂት ጊዜ ባሉበት ከቆዩ በኋላ አማጺው የሁቲ ሠራዊትና በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በሚያደርጉት ውጊያ ሳቢያ ተጠልለውበት ከነበረው ስፍራ ለቅቀው ወጡ።

በእስር ቤቱ የሚገኙት አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን የኮሮናቫይረስን ሰበብ አድርጎ የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን በጦርነት ከሚታመሰው ግዛቱ በኃይል ያሳደዳቸው ናቸው። ሁቲዎች ከየመን እንዲወጡ ሳዑዲዎች ደግሞ ወደ ግዛታቸው እንዳይገቡ በሚያደርሱት ጫና በርካታ የሞቱ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይናገራል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይም የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከሰሜናዊ የመን ማስወጣታቸውንና በፈጸሙባቸው ጥቃት መግደላቸውን አስታውቆ ነበር።

ድርጅቱ የተለያዩ ኢትዮጵያዊያንን በማናገር አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ጥቂት የማይባሉ ስደተኞች ተገድለዋል። ጨምሮም ከየመን "ወደ ሳዑዲ አረቢያ ድንበር የተባረሩት ስደተኞች በድንበሩ ጠባቂዎች ሌላ ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ በዚህም የተወሰኑ ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩት ወደ ተራራማ አካባቢ ሸሽተዋል" ብሏል።

ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ከየመን ወጥተው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደገቡ የኮሮናቫይረስ ክስተትን ተከትሎ አሁን ባሉበት እስር ቤት ውስጥ ስድስት ወር ሊሆናቸው ነው። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑት እነዚህ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ እስር ቤት ሳይሆን "የምድር ላይ ሲኦል ነው" ሲሉ ካሉበት ሆነው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, ZECHARIAS ZELALEM

የምስሉ መግለጫ,

በድብደባ የተጎዱ ስደተኞች

ከየመን በድንበር በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከገቡ በኋላ ግን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ቢያደርጉም የገጠማቸው ግን "ሲኦል" ወዳሉትና በችግርና በተለያዩ በሽታዎች ወደሚሰቃዩበት እስር ቤት "መወርወር" ነበር።

በዚህ እስር ቤት ውስጥ ስላለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የሚናገረው ቢቢሲ ያነጋገረው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ፣ በርካቶቹ በተለያዩ ህመሞች እየተሰቃዩ ይገኛሉ ብሏል።

እስር ቤቱ ከ20 የሚበልጡ ግቢዎች እንዳሉት ይነገራል። በየአንዳንዱ ግቢ ውስጥም 400 ያህል ስደተኞች በተጨናነቀና ንጽህናው ባልተጠበቀ ሁኔታ ታስረው እንደሚገኙ በአንደኛው ጊቢ ያሉት ስደተኞች ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች እንዳሉት እነሱ ባሉበት ቦታ ለወራት በር ተዘግቶባቸው ውጪውን እንዳላዩና፣ ካሉበት አስጨናቂ ሁኔታ የተነሳም ከኢትዮጵያዊያን መካከል ብዙዎቹ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ችግር እየገጠማቸው ነው። ከመካከላቸውም "ሁለቱ ካሉበት የስቃይ ህይወት የተነሳ ራሳቸውን አጥፍተዋል" ብለዋል።

በእስር ቤቱ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ቁጥርን በትክክል ባያውቁትም አስከ አራት ሺህ እንደሚደርስ ይገምታሉ። ከእነዚህም ውስጥ ሴቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ ነገር ግን በተለየ እስር ቤት ውስጥ ስላሉ ያሉበትን ሁኔታ እንደማያውቁ ይናገራሉ።

ሴቶች ታስረው ከሚገኙበት በአንዱ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ቢቢሲ ለማግኘት ችሎ ነበር፤ ምንም እንኳን በአንድ ግቢ ውስጥ እንደ ወንዶቹ በመቶዎቹ ሆነው በተጨናነቀ ሁኔታ ባይታሰሩም ሙቀቱና የንጽህናው ሁኔታ ተመሳሳይ እንደሆነ ይናገራሉ።

ለወራት በእስር ቤቱ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ በመቆየታቸው ልብሳቸው ላያቸው ላይ አልቆ መራቆታቸውን የምትናገረው ለቢቢሲ ቃለወን ሰጠችው ግለሰብ፣ የንጽህና ችግርና እሱን ተከትሎ የሚጣው የቆዳ በሽታ እያሰቃያቸው መሆኑን ገልጻለች።

በሴቶቹ እስር ቤት ውስጥ ጥቂት ህጻናትና ነፍሰጡር እናቶች መኖራቸው ገልፀው፣ እነዚህ ሴቶችና ህጻናት ጤናና ሕይወት አደጋ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ቢሆንም ግን አልፎ አልፎ ህክምና እንዲያገኙ እንደሚደረግ ቢገልጹም የሚሰጣቸው መድኃኒት ለፈውስ የሚሆን ሳይሆን የተለመደ የህመም ማስታገሻ ነው ብለዋል።

ሴቶቹ ለእስር ቤቱ ኃላፊዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሷቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የእስር ቤቱን ተጠሪዎች ቢወተውቱም "ይህ የሚመለከተው የአገራችሁን መንግሥት ነው" የሚል ምላሽ እንዳገኙ በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያደርግላቸው የሚችለውን ነገር በጉጉት ሲጠብቁ ወራት እንዳለፋቸው አንደኛዋ ስደተኛ ለቢቢሲ ተናግራለች።

የምስሉ መግለጫ,

በእስር ቤቱ በተስፋፋው የቆዳ በሽታ ብዙዎቹ ተጠቅተዋል

ከዚህ ቀደም አንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካይ ወደ እስር ቤቱ መጥቶ እንዳናገራቸውና መንግሥት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽላቸውም ምንም ነገር ሳይሰሙ "የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል" በማለት ከዚያ በኋላ ስላሉበት ሁኔታ መጥቶ የተመለከተም ሆነ ያየ እንደሌለ ጠቅሳለች።

ሁሉም ኢትዮጵውያን ወጣቶች በሞትና በሕይወት መካከል በአደገኛ ሁኔታ በመጓዝ ወደ ሳኡዲ አረቢያ የገቡት ጉልበታቸውን አፍስሰው ሥራ በመስራት የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለመለወጥ በማለም ነበር።

በሴቶቹ እስር ቤት ካሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል አንዷ የሆነችው *መሰረት ልጆቿን ለማስተማርና ለማሳደግ እንዲሁም በእድሜ የገፉ ወላጆቿን ሳዑዲ ውስጥ ሰርታ ለመጦር "ብዙ ብር ከስክሳ" ብትመጣም ከወራት በፊት ተይዛ ወደ እስር ቤት በመግባቷ ግራ መጋባት ውስጥ እንዳለች ትናገራለች።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች መጥተው አብረዋት ያሉት ሴቶችም ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሲሆን፣ ያቀዱት ባለመሳካቱና ለቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ከመሆን ይልቅ እንዲሁ በእስር ቤት ባክነው መቅረታቸው ህሊናቸውን እየረበሸው በመሆኑ ብዙዎቹ በጭንቀት ላይ ናቸው ትላለች።

ነገር ግን በጦርነትና በበሽታ መካከል አልፈው የተረፉት ሳዑዲ አረቢያ ቢገቡም ለወራት የታሰሩበት እስር ቤት ውስጥ ከሞት ጋር እንዲፋጠጡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። በከፍተኛ ሙቀትና ከንጽህና ጉድለት ተነሳ ለተለያዩ በሽታውች በመጋለጣቸው ሕይወታቸውን ለአደጋ ማጋለጡን ይናገራሉ።

"እስር ቤቱ ጽዳት የለውም፣ ሽንት ቤቶች ሞልተው ፍሳሹ ወደ ክፍሎቹ ይገባል፣ ከእከክ ጋር የሚመሳሰል የቆዳ በሽታ ሁሉንም እሰረኞች ይዟል" በዚህም ሳቢያ በርካቶቹ እንቅልፍ እንደማይወስዳቸውና ፊታቸው ሳይቀር እያበጠ መቸገራቸውን ከእስረኞቹ አንዱ ለቢቢሲ ገልጿል።

በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆነው ህክምና ቢጠይቁም ማግኘት አዳጋች ነው ይላሉ። ሲበረታባቸውም ምግብ በሚቀርብበት ወቅት ስለንጽህናቸውና ስለህክምና ጥያቄ በሚቀርቡበት ጊዜ በጥበቃዎቹ ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው ይናገራሉ። ከእስር ቤቶቹ የወጡ ፎቶዎችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው።

ኢትዮጵያዊያኑ ወደእዚህ እስር ቤት የገቡት ወንጀል ሰርተው እንዳልሆነ የሚናገረው አብዱ "ሰርተን ለእኛም ለቤተሰቦቻችንም የተሻለ ነገር እናደርጋለን ብለን ነበር ከአገር የወጣነው። ግን ኮሮና መጥቶ ያሰብነው ሳይሳካ ወደ እስር ቤት ገብተናል" በማለት የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጿል።

ሳኡዲ ውስጥ ወደ ሚገኙት እነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ ሲገቡ በአጭር ጊዜ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ እንደተነገራቸው የሚያስታውሱት ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች፣ አሁን ግን ካሉበት ሁኔታ አንጻር በህይወት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስለመቀላቀላቸው እርግጠኛ አይደሉም።

"የሳዑዲም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘንግቶናል፤ ለዚህም ነው በምድር ላይ ባለ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ በሕይወት የምንቆይበትን ቀን እየቆጠርን ያለው" ሲል አብዱ በምሬት ይናገራል።

መሰረትና አብዱ አሁንም ተስፋ አልቆረጡም የመጨረሻ ተስፋቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መሆኑን ይናገራሉ። ከዛሬ ነገ "ከዚህ ሲኦል ወጥተን ቢርበንም ቢጠማንም በችግር ወደ ምንኖርበት አገራችን ተመልሰን፣ የቤተሰቦቻችን አይን ማየት ነው ተስፋችን" ይላሉ።

አብዱ እናትና አባቱ ሁሉንም ትቶ እንዲመለስ ይፈልጋሉ፤ እሱ እንደሚለውም "እነሱን እደግፋለሁ ብዬ ወጥቼ በተቃራኒው በደካማ ጎናቸው እነሱ ስለእኔ በመጨነቅ እየተጎዱ ነው" ይላል።

የታዳጊ ልጆቿን ሕይወት የሰመረ ለማድረግ የተሰደደችው መሰረትም "ከሁሉ በላይ የናፈቀኝ የልጆቼን አይን ማየት ነው" ትላለች በእስር ቤቱ ያለው ሁኔታ ስላላስተማመናት።

በሳዑዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በተመለከተ ያላቸውን አስተያየት ለማግኘት በስልክ በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው ሳይሳካልን ቀርቷል።

ይህንን የስደተኞቹን ስቃይና ሰቆቃ በተመለከተ 'ዘ ቴሌግራፍ' የእንግሊዝ ጋዜጣ በዝርዝር መዘገቡን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሳዑዲ መንግሥት የስደተኞቹ አያያዝ ላይ ጥያቄ በማንሳት ድርጊቱን አውግዘውታል።

ይህንንም ተከትሎ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ለንደን በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ለጋዜጣው በሰጠው ምላሽ "ከቀረበው ክስ አንጻር በመንግሥት በሚተዳደሩት እስር ቤቶች ውስጥ በሙሉ ስላለው ሁኔታ ምርመራ" እያደረገ መሆኑን ገልጾ "በእርግጥም አስፈላጊው ነገሮች የተጓደለ ሆኖ ከተገኘ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል" ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ [ሐሙስ] ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ እየሰራ መሆኑንና የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር በሪያድ የሚገኘው ኤምባሲው እንዲሁም በጅዳ ያለው ቆንስላ ሙሉ ትኩረቱን ለዚሁ ጉዳይ መስጠቱን አስታውቋል።

ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ 2012 ባሉት ወራት 3500 ዜጎች ከሳዑዲ እንዲመለሱ መደረጉም ሚኒስቴሩ ተጠቅሷል። አሁንም ከጰጉሜ 3/ 2012 እስከ መስከረም 28/2013 ባሉት ቀናት ቅድሚያ የተሰጣቸው 2ሺህ ስደተኞችን ወደ አገር እንደሚመለሱም ተጠቁሟል።

ስደተኞችን ወደ አገር ቤት የመመለሱ ሥራው የተለያዩ የፌደራል ሚንስቴር መስሪያ ቤቶችን፣ ኤምባሲዎችን እና የክልል ቢሮዎችን በቅንጅት የሚሰሩት ነው ብሏል።

በዚህም መሰረት አገሪቱ በውጭ አገራት በስደት ላይ ያሉ ዜጎቿን አልቀበልም ብላ እንደማታውቅ ገልጾ በተቻለ አቅም ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እንዲመረሱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልከቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየገቡ ያሉ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

* ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሰቆቃ በሳኡዲ አረቢያ እስርእ ቤቶች