በምስራቅ ጎጃም ዞን በአዋበል ወረዳ የመሬት መንሸራተት ጉዳት አስከተለ

የመሬት መንሸራተት

የፎቶው ባለመብት, Awabel communication info

በምስራቅ ጎጃም ዞን በአዋበል ወረዳ በሰባት ቀበሌዎች በደረሰው የመሬት መንሸራተት ሰብሎችን ለውድመት ህብረተሰቡን ደግሞ ለችግር ዳርጓል፡፡

በመሬት መንሸራተቱ 135 ቤቶች ሲፈርሱ 336 አባውራዎች በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ 1260 ሰዎች ለችግር ተጋልጠዋል።

ጉዳቱ የደረሰባቸው አካባቢዎች ሚዛን፣ ጡረት፣ ለጋ የጠረብና፣ ጅት ባህር፣ ወጀል አንቅራቅ፣ እነቢ ጭፋር እና አዲስ አምባ ጨሊያ መሆኑ ታውቋል።

መምህር ተመስገን አጥናፉ የሚዛን ነዋሪ ሲሆኑ እያቄም የምትባለውና እና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን ጎጥ በቦታው በመሄድ መመልከታቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

የመሬት መንሸራተቱ ነሐሴ 22/2012 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 አካባቢ መከሰቱን አስታውቀው ከ100 በላይ ቤቶች የፈረሱ መሆኑን ገልጸዋል።

"አንዳንዶች 'ቤታችሁ የት ነው?' ተብለው ሲጠየቁ ራሱ ቤታቸው የት እንደሆነ የት አካበቢ እንደሆነ ራሱ አያውቁትም" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።

ቤቶቹ ከእነ ሙሉ ዕቃቸው መፍረሳቸውን ገለጸው አብዛዎቹ ነዋሪዎች ቤት ዘግተው ሥራ ላይ እንደነበሩ እና አደጋው አስከፊ መሆኑን መመልከታቸውን አስታውቀዋል።

በቦታው በደረሱበት ወቅትም ዛፎች እተንሸራተቱ ሲወድቁ መመልከታቸውንም ገልጸውልናል። "ላይ ነበረው መሬት ወደታች ሄዶ እፈርሳል ይሰነጣጠቃል" ብለዋል።

በሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ባይሰሙም ከብቶች እና ፍየሎች ላይ ግን ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል። የፍየል ግልገሎች ላይ ቤት ፈርሶባቸው መመልከታቸውንም ጠቅሰዋል።

አካባቢው አትክልት እና ፍራፍሬ በብዛት የሚለማበት መሆኑን ጠቅሰው የደረሰውን አደጋ "እኔ እንዲህ አይነት አስከፊ ሁኔታ ገጥሞኝም አይቼም አላውቅም በህይወቴ" ሲሉ ገልጸውታል።

በአዋበል ወረዳ ሰባት ቀበሌዎች ከነሀሴ 22/2012 ጀምሮ የመሬት መንሸራተት መከሰቱን ደግሞ የወረዳው የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ አቶ አቶ አስማማው አሰፋ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የደረሰው ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ተለይቶ አለመጠናቀቁን አስታውቀው በመሬት መንሸራተቱ 336 አባወራዎች ጉዳት ሲደርስባቸው 135 ቤቶች ደግሞ ፈርሰዋል ብለዋል።

ስልሳ የሚጠጉ ተጨማሪ ቤቶች የመፍረስ አደጋ የተደቀነባቸው ሲሆን ከ125 እስከ 135 ሄክታር የሚደርስ መሬት ላይ ያለ ሰብል እና 135 ሔክታር ላይ ያለ አትክልትና ፍራፍሬ ጉዳት ሲደርስበት ከብቶች እና ፍየሎችም ሞተዋል ብለዋል።

ሚዛን ዋሻ ቱሉ በምትባል ቀበሌ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ እያቄም በምትባል ጎጥ የነበሩ ቤቶች፣ ሰብል፣ አትክልታና ፍራፍሬ እንዲሁም በገተራ ውስጥ ነበረ እህል ሙሉ ለሙሉ መውደሙን አስታውቀዋል።

አደጋው ነሐሴ 22 የጀመረ ቢሆንም ዛሬም ድረስ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንደተከሰተ አስታውቀዋል።

"አደጋው እየሰፋ ነው። እስከ ትላንት 119 ቤቶች ነበር ጉዳት የደረሰባቸው። ትላንት ከሰዓት እና ዛሬ ነው ቁጥሩ 135 ደረሰው። የመሬት መንሸራተቱ አሁንም አለ እየቀጠለ ነው። ወደ አካባቢው ሄደን ባናጣራም ዛሬ ሌሎች 2 ቀበሌዎች ተጨምረዋል የሚል ነገር አለ" ብለዋል።

የመሬት መንሸራተቱ በዝናብ መብዛት ምክንያት ከፍተኛ ውሃ መሬት ውስጥ ስለላ ነው የተከሰተው ያሉት አቶ አስማማው ቤቶችን እስከ 15 ሜትር ድረስ በመውሰድ ከጥቅም ውጭ አድርጓል ብለዋል።

ቤት ንብረታቸውን ያጡ ሰዎችን በዘመዶቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው እና እንደ ትምህርት ቤት ባሉ የመንግስት ተቋማት መጠለላቸውን ጠቁመዋል።

እስካሁን ከህብረተሰቡ ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን እና የወረዳው የቴክኒክ ኮሚቴ ቦታው ድረስ ሄዶ ችግሩን በመመልከት ተጎጂዎችን ጋር መነጋገሩን ጠቁመዋል።

ኮሚቴ የምግብ እና አልባሳት ቁሳቁስ ድጋፍ ለመስተት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸው መንግስት እና ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል።