በቻርሊ ሄብዶ ጥቃት ተባባሪ ናቸው የተባሉ ለፍርድ ቀረቡ

ቻርሊ ሄብዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፈረንጆቹ 2015 ፈረንሳይ በሚገኘው ቻርሊ ሄብዶ የተሰኘ ስላቃዊ ይዘት ያለው ጋዜጣ መሥሪያ ቤት ላይ ለደረሰው ጥቃት ተባባሪ ናቸው የተባሉ 14 ሰዎች ችሎት ውለዋል።

አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች ፓሪስ የሚገኝ ፍርድ ቤት በአካል ሲቀርቡ 3 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በሌሉበት ጉዳያቸው እየታየ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ኢስላማዊ ታጣቂዎች በጋዜጣው አዘጋጆች ላይ ጥቃት እንዲያደርሱ ተባብረዋል፤ 12 ሰዎች እንዲገደሉም ምክንያት ሆነዋል ተብለው ነው የተከሰሱት።

በተያያዘ ጥቃት በወቅቱ አንድ ታጣቂ ፖሊስ ገድሎ ሲያበቃ ወደ አንድ አይሁድ መደብር አቅንቶ ሌሎች አራት ሰዎችን ገድሏል።

ጥር 2015 ላይ ፈረንሳይን ባሸበረው በዚህ ጥቃት በሶስት ቀናት ውስጥ 17 ሰዎች ተገድለዋል። ይህ ጥቃት በፈንሳይ በጂሃዲስቶች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ያቀጣጠለ ሲሆን በድምሩ 250 በተለያዩ ወቅቶች በጂሃዲስቶች በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል።

እነዚህን ተከታታይ ጥቃቶች ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፈረንሳውያንና የሌሎች ሃገራት ዜጎች 'ጀ ስዊ ቻርሊ’ [እኔ ቻርሊ ነኝ] የሚል መፈክር ያለው ተቃውሞ አሰምተዋል።

ጋዜጣው የፍርድ ሂደቱ መጀመሩን አስመልክቶ ነብዩ ሞሐመድን የተመለከተ አነጋጋሪ የካርቱን ምስል አትሟል። ይህ ምስል በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይ ባላቸው ሃገራት ዘንድ ቁጣን ጭሯል።

ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማክሮ ይህንን ተከትሎ ፈረንሳይ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት ቦታ አለው ሲሉ ተከላክለዋል።

ችሎቱ ላይ ምን እየተባለ ነው?

11 ተጠርጣሪዎች ዕለተ ረቡዕ በተሰየመው ችሎት ላይ ተገኝተዋል። ስማቸውንና የሥራ መስካቸውን ከጠቀሱ በኋላ ለፍርድ ቤቱ ላለመዋሸት ቃል ገብተዋል።

የፍርድ ሂደቱ ቢያንስ ለ4 ወራት የዘገየው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ነው።

በፍርድ ቤቱ ዙሪያ ጠንከር ያለ የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ ይስተዋላል።

በጥቃቱ ተባብረዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች የጦር መሣሪያ በመያዝና ለጥቃቱ አስፈላጊ መረጃዎችን በመስጠት ነው የተከሰሱት።

ጥቃቱ ቻርሊ ሄብዶ በተሰኘው ስላቃዊ ጋዜጣ፣ በፖሊስና ሃይፐር ካሸር የገበያ ማዕከል ላይ ነው የተፈፀመው።

በሌሉበት ፍርዳቸው እየታየ ያሉ ሶስት ተጠርጣሪዎች ወደ ሶሪያና ኢራቅ ሳይገቡ እንዳልቀረ ይጠረጠራል። ዘገባዎች እንደሚሉት ሁለቱ ኢስላሚክ ስቴት [አይኤስ] ላይ በተወሰደ የቦንብ ጥቃት ሳይሞቱ አልቀሩም።

200 ያክል ከሳሾችና ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ምስክርነታቸውን ለመስጠት ችሎት ተገኝተዋል።

ባለፈው ሰኞ ፀረ-ሽብር አቃቤ ሕግ ዢን ፍራንኳ ሪካርድ ‘ለፍርድ የቀረቡት ጥቃቅን እርዳታ ያደረጉ ሰዎች ናቸው’ መባሉን ተቃውመዋል።

በችሎቱ ላይ ከተገኙት መካከል የገበያ ማዕከሉ ሠራተኛ የነበረው ማሊየተወለደው ሙስሊሙ ላሳን ባቲሊ አንዱ ነበር። ግለሰቡ በወቅቱ በርካታ ሸማቾን ደብቆ ከጥቃት በማትረፉ ምስጋና ተችሮታል፤ የፈረንሳይ ዜግነትም አግኝቷል።

የፍርድ ሂደቱ እስከ ወርሃ ኅዳር ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ይገመታል።

ተጠርጣሪዎች ከባድ ጥበቃ እየተደረገላቸው በአንድ የመስታወት ክፍል ውስጥ ሆነው ነው ፍርዳቸውን እየተከታተሉ ያሉት። ሁሉም ተጠርጣሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድረጋቸው ምክንያት ፊታቸው ላይ ያለውን ስሜት ማንበብ አልተቻለም።

በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች ጥቃቱ እንዴት እንደተቀነባበረ ማወቅ ይሹ ነበር።

2015 ላይ ምን ተፈጠረ?

በፈንረጆቹ 2015 ሁለቱ ወንድማማቾች ሸሪፍ እና ሰዒድ ኩዋቺ የቻርሊ ሄብዶ ጋዜጣ ቢሮን ጥሰው ገቡ። አረንጓዴ የወታደር ልብስ አድርገው የነበሩት ወንድማማቾች የጋዜጣው ሠራተኞች ላይ ጥይት ማርከፍከፍ ጀመሩ።

በወቅቱ የጋዜጣው አርታኢ የነበረው ግለሰብን ጨምሮ ሌሎች አራት ሰራተኞች ወዲያው ተገደሉ።

ከቆይታ በኋላ ፖሊስ ሥፍራውን ቢከብም በጥቃቱ ማብቂያ ስምንት ጋዜጠኞችና ሁለት የፖሊስ መኮንኖች መሞታቸው ይፋ ሆነ።

ከቀናት በኋላ በተፈፀመ ሌላ ጥቃት ደሞ ሃይፐር ካሸር የተባለ ገበያ ውስጥ ተኩስ የከፈተው አመዲ ኩሊባሊ የተሰኘ ጂሃዲስት ሶስት ሰዎችን ገደለ። ሰውዬው ወደ ገበያው ከመምጣቱ በፊት አንድ የፖሊስ መኮንን ገድሎ ነበር።

ፖሊስ ወደ ገበያው ከደረሰ በኋላ ጂሃዲስቱን ገድሎ ታግተው የነበሩ ሰዎችን አስለቀቀ።

በጥቃቱ እጃቸው አለበት የተባሉ ሰዎች አብዛኛዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።