ጀርመን የፑቲን ተቃዋሚው መመረዙን አረጋገጥኩ አለች

አሌክሴ ኖቪቾክ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን በድፍረት በመተቸት የሚታወቀው አሌክሴ ናቫልኒ ‘ናቪቾክ’ በሚሰኝ የነርቭ ስርዓትን በሚያውክ መርዝ መመረዙን የጀርመን መንግሥት ይፋ አደረገ።

የላብራቶሪው ምርመራ ውጤት ናቪቾክ ስለመመረዙ ማረጋገጫ ነው ሲሉ የአሌክሴ ናቪቾክ ደጋፊዎች ተናግረዋል።

የጀርመን መንግሥት አሌክሴ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገልጾ፤ ሩሲያ በአስቸኳይ ማብራሪያ እንድትሰጥ ጀርመን ጠይቃለች።

መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል በጉዳዩ ላይ ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር አስቸኳይ ስብሰባ መቀመጣቸውም ተነግሯል።

የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን በድፍረት በመተቸትና በማብጠልጠል የሚታወቀው አሌክሴ ናቫልኒ ድንገተኛ ህመም ካጋጠመው በኋላ ለህክምና ወደ ጀርመን መወሰዱ ይታወሳል።

አሌክሴ ናቫልኒ ነሐሴ 15 ቶምስክ ከምትሰኝ የሩሲያ ከተማ ወደ መዲናዋ ሞስኮ እየበረረ ሳለ ከፍተኛ ሕመም ስለተሰማው አውሮፕላኑ በድንገት ኦምስክ፣ ሳይቤሪያ እንዲያርፍ ተገዶ ነበር።

አሌክሴ አውሮፕላኑን ከመሳፈሩ በፊት በቶምስክ አውሮፕላን ጣቢያ ቁጭ ብሎ ሻይ ሲጠጣ የሚያሳይ ፎቶ ተለቆ ነበር።

ይህም ለህመሙ ምክንያት መመረዙ ነው የሚሉ ግምቶች በስፋት ተዛምቷል።

የሩሲያ መንግሥት ግን ይህን ወቀሳ በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።

የአሌክሴ የመታመመዝ ዜና ከተሰማ በኋላ ጀርመን የአውሮፕላን አምቡላንስ ወደ ሩሲያ ልካ አሌክሴን ለተጨማሪ ሕክምና ወደ በርሊን ማምጣቷ ይታወሳል።

አሌክሴ ለህመም ከተዳረገ በኋላ ለበርካታ ቀናት በቬንትሌተር እገዛ ሲተነፍስ ቆይቷል።

አሌክሲ ናቫልኒ ማን ነው?

አሌክሴ በሩሲያ ውስጥ እውቅና ያገኘው የባለሥልጣናትን ሙስና በማጋለጥ ነው። በዚህም በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። የፑቲንን ፓርቲ የሞሉት ሸፍጠኞችና ሌቦች ናቸው ይላል አሌክሲ።

በ2011 የፑቲን ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ምርጫ አጨበርብሯል ብሎ በማጋለጡ ለ15 ቀናት ታስሮ ነበር። በ2013 አሌክሴ በሙስና ክስ ተመስርቶበት ለአጭር ጊዜ ከታሰረ በኋላ ተለቋል።

በ2018 ፑቲንን ለመገዳደር ምርጫ ቅስቀሳ ቢጀምርም ቀደም ሲል በነበረበት የምዝበራ ክስ ምክንያት መወዳደር አትችልም በሚል ታግዷል። በ2019 ፑቲንን የሚቃወም ትልቅ ሰልፍ በመጥራቱ ሕገ-ወጥ የሰልፍ ጥሪ አድርገሀል በሚል ለ30 ቀናት ታስሯል።

ያን ጊዜ በእስር ላይ ሳለ ባልተለመደ ሁኔታ ሕመም ገጥሞት ነበር። ሐኪሞች የቆዳ አለርጂ የሚመስል ነገር ቢጠቅሱም እሱ ግን አለርጂ ኖሮበት እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር።

በኋላ ላይ ግን የገዛ ሐኪሞቹ ለአንዳች መርዝነት ላለው ነገር ተጋልጠህ ነበር ሲሉ ነግረውታል።ምናልባት እስር ቤት ሳለ እሱን መርዞ ለመግደል ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ይገመታል።

ቪላድሚር ፑቲን ከዚህ ቀደም በርከት ያሉ ተቃዋሚዎቻቸውን፣ የስለላ መኮንኖችን፣ ጋዜጠኞችን በጠራራ ጸሐይ በማስገደል እና በሰው አገር ጭምር ሄደው በመመረዝ ስማቸው ይነሳል።