የቻይና ስም በደቂቅ የተፃፈበት አዲሱ የታይዋን ፓስፖርት

የታይዋን አዲሱ ፓስፖርት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

የታይዋና የቀድሞ ፓስፖርት (ግራ) እና አዲሱ ፓስፖርት (ቀኝ)

የታይዋን ባለሥልጣናት አዲስ ፓስፖርት ይፋ አድርገዋል።

ፓስፖርቱ ‘ታይዋን’ የሚል በደማቅ የተፃፈበት ሲሆን ‘ሪፐብሊክ ኦፍ ቻይና’ የሚለው በደቃቅ ፅሑፍ ታትሞ ይታያል።

ባለሥልጣናቱ ይህን ያደረግነው የታይዋን ዜጎች ከቻይና ዜጎች ጋር እንዳይምታቱ በማሰብ ነው ብለዋል።

ደሴቲቱ ነፃ ሃገር ነኝ ብትልም ቻይን ግን እራሷን ከቻይና ለመገንጠል ጥረት የምታደርግ ግዛት አድርጋ ነው የምትቆጥራት።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አዲሱ ፓስፖርት ታይዋንን ‘የቻይና አንድ ክፍል ከመሆን የሚያተርፋት አይደለም’ ብለዋል።

የታይዋን ባለሥልጣናት ዕለተ ረቡዕ ደመቅ ባለ ሥነ-ሥርዓት ነው አዲሱን ፓስፖርት ያስተዋወቁት።

የታይዋን ኦፌሴላዊ መጠሪያ የሆነው ‘ሪፐብሊክ ኦፍ ቻይና’ ከፓስፖርቱ ሽፋን ላይ ተነስቶ በምትኩ 'ታይዋን' የሚለው ስያሜ በትላልቅ ፊደላት ሰፍሯል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረ ወዲህ ‘ዜጎቻችን ጎልተው እንዲታዩና ከቻይና ዜጎች ጋር እንዳይምታቱ እየሰራን ነው’ ሲሉ የታይዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሴፍ ዉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል በርካታ ሃገራት ከቻይና የሚመጡ ሰዎች ላይ እግድ በመጣላቸው ምክንያት ይህንን ለማስወገድ የተደረገ እርምጃ መሆኑን ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

በተለይ ከኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ በኋላ ታይዋን ከቻይና ጋር የለየለት ጠብ ገጥማለች።

ታይዋን ወረርሽኙን በተቆጣጠረችበት መንገድ ከበርካታ መንግሥታት አድናቆት ብታገኝም የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት አባል ሃገር ግን አይደለችም።

ቻይና፤ ታይዋን ከድርጅቱ እንቅስቃሴዎች ያገደቻት ከ2016 [በአውሮፓውያኑ] ጀምሮ ነው።

ታይዋን ከአውሮፓውያኑ 1949 ጀምሮ ራሷን በራሷ ስታስተዳድር ቆይታለች። የራሷን ዴሞክራሲያዊ ምርጫም ታካሂዳለች። የራሷ የሆነ ጦር ሠራዊትና የመገበበያ ገንዘብም አላት።

ነገር ግን በአንድ ቻይና ፖሊሲ መሠረት ቻይና ታይዋንን የራሷ ግዛት አድርጋ ትቆጥራታለች። አንድ ቀን የታይዋን ግዛት ወደ ቻይና ትመጣለች - አስፈላጊ ከሆነም በኃይል ትላለች ቻይና።

የታይዋን ፕሬዝደንት ሳይ ኢንግ-ዌን ቻይና ‘እውነታን እንደትቅበልና’ ለታይዋን ክብር እንድታሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የተወሰኑ የዓለማችን ሃገራት ታይዋንን እንደ ሃገር ይቆጥሯታል። ነገር ግን እንዲህ ያደረጉ ሃገራት በቻይና ጥርስ ተነክሶባቸዋል።

በቅርቡ አንድ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ታይዋንን መጎበኝታቸው አይዘነጋም።