ሄሪ እና ሜጋን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሊጀምሩ ነው

ሃሪ እና ሜጋን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ሃሪ እና ሜጋን

የሰሴክስ መስፍን እና ሶፋኒት ከግዙፉ የቴሊቪዥን ፕሮግራሞች እና ፊልሞች ማሳያ ኔትፍሊክስ ጋር በመሆን የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት ተስማሙ።

በአንዳንዶቹ ፕሮግራሞች ላይ ሄሪ እና ሜጋን እራሳቸው ይታዩበታል ተብሏል።

“ትኩረታችን አስተማሪ እና ተስፋ የሚሰጡ ይዘቶችን ማዘጋጀት ነው” ብለዋል ሄሪ እና ሜጋን።

“እንደ አዲስ ወላጆች አነቃቂ የቤተሰብ ይዘት ያላቸው ይዘቶችን ማዘጋጀት ለእኛ አስፈላጊ ነው” ሲሉም ጨምረዋል።

የኔትፍሊክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴድ ሳራንዶስ ጥንዶቹ ኔትፍሊክስን በመምረጣቸው “ከፍተኛ ኩራት” ተሰምቶኛል ብለዋል።

ከሁለት ዓመታት በላይ በሚዘልቀው ውል ጥንዶቹ ከኔትፍሊክስ ጋር ፊልሞችን፣ ዘጋቢ ፊልሞችን እና የህጻናት ፕሮግራሞችን ያዘጋጃሉ ተብሏል።

ሃሪ እና ሜጋን የንጉሳዊ ህይወት ይቅርብን ብለው መኖሪያቸውን በአሜሪካ እና ካናዳ መካከል ካደረጉ ከስድስት ወራት በኋላ ነው ከኔትፍሊክስ ጋር የደረሱት ስምምነት የተሰማው።

የሰሴክሱ መስፍን ኔትፍሊክስ ላይ ለእይታ እየበቃ ባለው ‘ራይዚንግ ፊኒክስ’ በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ ይታያል።

ሜጋንም እንዲሁ ‘ሱትስ’ በሚሰኘው ተከታታይ ፊልም ላይ ስትተውን ትታያለች።

ሜጋን ሜርክልና ሃሪ የቤተ-መንግሥት ኃላፊነት ይብቃን ማለታቸው የተሰማው ከወራት በፊት ነበር።

ሜጋንና ሃሪ ውሳኔውን የወሰኑት የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብን ሳያማክሩ ነበር።

የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ልዑላን ምንም እንኳ ስለ ሜጋንና ሃሪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመምከር ላይ የነበሩ ቢሆንም ይህንን ውሳኔ አልጠበቁትም ነበር ተብሏል።

ባልና ሚስቱ ከነባር የቤተ-መንግሥት ኃላፊነታቸው ወርደው በገንዘብ ራሳቸውን ለመቻል እንደሚጥሩ መናገራቸው ይታወሳል።